ቀጥታ፡

በአርባ ምንጭ ከተማና ሀዲያ ዞን ክልከላዎችን የጣሱ 162 ንግድ ድርጅቶችና ግለሰቦች ተቀጡ

አርባምንጭ፣ ሆሳዕና ሰኔ 6/2012 (ኢዜአ) በአርባምንጭ ከተማና ሀዲያ ዞን ወረርሽኙን ለመከላከል የወጣውን አዋጅ ክልከላዎች ተላልፈው የተገኙ 162 የንግድ ድርጅቶችና ግለሰቦች ተቀጡ።

የአርባምንጭ ከተማ የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አባልና የንግድና ገበያ ልማት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ዮርዳኖስ ወንድይፍራው እንደገለጹት ክልከላውን በመጣስ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ጤፍ ምርት ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ 42 የንግድ ድርጅቶችን እጅ ከፍንጅ ተደርሶባቸዋል። 

እነዚህን ጨምሮ ወረርሽኙን ሊያስፋፉ የሚችሉ 81  መሸታ፣ ጫት ማስቃሚያና ሺሻ ማስጨሻ፣ ዲኤስ ቲቪ እና ፑል ማጫወቻ ቤቶች ደግሞ ክልከላውን በመተላለፍ ተገኝተዋል።

ጥፋተኛነታቸው በማስረጃ በመረጋገጡ ሁሉም የንግድ ድርጅቶች በማሸግ እንዲቀጡ መደረጉን ኃላፊ አስታውቀዋል።


ወረርሽኙን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በአቋራጭ ለመበልጸግ በሚሯሯጡ ስግብግብ ነጋዴዎች ላይ የሚወሰደው ርምጃ ቀጣይነት ይኖረዋል።


በጽሕፈት ቤቱ የሸማቾች ጥበቃና ድጋፍ ሥራ ሂደት አስተባባሪ ወይዘሮ ሠናይት ዘሪሁን በበኩላቸው እየተባባሰ የመጣውን የዋጋ ንረት ለመከላከል የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራትን ለማሳተፍ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።  


"ወረርሽኙን ተከትሎ በርካታ ነጋዴዎች የዋጋ ጭማሪ ሲያደርጉ አይቼ እኔም ጭማሪ በማድረጌ መደብሬ ሊዘጋ ችሏል" ያሉት ደግሞ የሽንኩርት ነጋዴ አቶ ሰይፉ ደምሴ ናቸው።


ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ ሕገወጥ ተግባር መሆኑን በማመን ለጽሕፈት ቤቱ የይቅርታ ማመልከቻ በማስገባት ምላሽ እየጠበቁ መሆኑን ተናግረዋል። 


በአርባ ምንጭ ከተማ የዕድገት በር ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ አልማዝ ጌታቸው በሰጡት አስተያየት ወረርሽኙን ተከትሎ እየተደረገ ባለው የዋጋ ጭማሪ በኑሯችን ላይ ጫና ማሳደሩን ተናግረዋል። 


በተለይ 24 ብር የነበረው የአንድ ኪሎ ግራም ሽንኩርት ዋጋ 35 ብር፣ 16 ብር የነበረው የቲማቲም ዋጋ 25 ብር፣ 33 ብር የነበረው የአንድ ኪሎ ጤፍ ዋጋ ደግሞ ወደ 42 ብር በማሻቀቡ ሸምተው ለመጠቀም  መቸገራቸውን አመላክተዋል። 


መንግሥት የማይገባ ጥቅም ለማግኘት በሚንቀሳቀሱ ነጋዴዎች ላይ የጀመረው ቁጥጥርና ቅጣት አስተማሪ ስለሆነ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ፍላጎታቸው መሆኑን ገልጸዋል። 


በሌላ በኩል የተቀመጡ ክልከላዎችን የጣሱ 39 ግለሰቦችን በገንዘብ መቅጣቱን የግብረ ኃይሉ አባልና  የሀዲያ ዞን  ዓቃቤ ሕግ መምሪያ ኃላፊ አቶ ገቲሶ ዴታሞ አስታውቀዋል።


ግለሰቦቹ በሆሳዕና ከተማ፣ ምዕራብ ባደዋቾና አመካ ወረዳዎች ውስጥ በአንድ ቦታ ማሰባሰብ የሚከለክለውን ደንብ በመተላለፍ ጫት ሲያስቅሙ፣ የመዝናኛ አገልግሎት ሲሰጡና ከተፈቀደው የሰው ልክ በላይ በማሳፈር ሲያሽከረክሩ በመገኘታቸው እያንዳንዳቸው ከአንድ ሺህ እስከ አራት ሺህ ብር በሚደርስ ገንዘብ እንዲቀጡ መደረጉን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም