የትግራይ ክልል ምክር ቤት ከ13 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት አጸደቀ

41
መቀሌ ሰኔ 30/2010 የትግራይ ክልል ምክር ቤት የክልሉን የ2011 ዓ.ም. በጀት 13 ቢሊዮን 537 ሚሊዮን 072 ሺህ 882 ብር በማጽደቅ 12ኛ ጉባኤውን አጠናቀቀ። የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የ5ኛ ዘመን 12ኛ መደበኛ ጉባኤ ለ2011 ዓ.ም ዘመን የሚውል በጀትና የተለያዩ አዋጆችን በማጽደቅ ማምሻውን ተጠናቋል። ምክር ቤቱ የክልሉን የ2011 ዓ.ም. በጀት 13 ቢሊዮን 537 ሚሊዮን 072 ሺህ 882 ብር  እንዲሆን በመወሰን አጽድቋል። ከዚህ ውስጥም ለመደበኛ 2 ነጥብ 8  ቢሊዮን፣ ለካፒታል በጀት 2ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር እንዲሆን የወሰነ ሲሆን ለገጠር ወረዳዎች አምስት ቢሊዮንና ለከተሞች አንድ ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር መድቧል። ከተመደበው በጀት 52 ነጥብ 8 በመቶ ለድህነት ተኮር ስራዎች የሚውል ሲሆን በዋነኛነትም ለውሃ ሃብት ልማት ፣ለኮንስትራክሽንና መንገድ ፣ እንዲሁም ለግብርናና ለገጠር ልማት ስራዎች የሚውል ነው ተብሏል። የበጀት ምንጩ ከፌዴራል መንግስት በድጎማና ለዘላቂ  ልማት ግቦች ማስፈፀሚያ ፣ እንዲሁም ከክልሉ ከሚሰበሰብ ገቢና ከተለያዩ የውስጥ ገቢዎች እንደሚሆንም ተመልክቷል። በዛሬው ውሎው ለምክር ቤቱ ተጠሪ የሆኑ ተቋማትን ዓመታዊ አፈጻጸም ሪፖርት በመገምገም ያጸደቀ ሲሆን በፍትሐብሔር ህግ ላይ የዳኝነት ክፍያን ለማሻሻል የተዘጋጀውን እንዲሁም በአሳ ሃብት ልማት አጠቃቀምና ጥበቃ ላይ የወጡትን ሁለት አዋጆች አጽድቋል። ምክር ቤቱ ከዚህ በተጨማሪ የስነ-ምግባር ግድፈት አለባቸው ያላቸውን የሁለት ዳኞችን ሹመት በማንሳት መደበኛ ጉባኤውን ዛሬ ማምሻውን አጠናቋል ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም