አዲስ አበባ ከተማ ከቆሻሻ አወጋገድ ችግር አለመላቀቋ ተገለፀ

79
አዲስ አበባ ሰኔ 30/2010 የአዲስ አበባ ከተማ  የቆሻሻ አስተዳደርና አወጋገድ ስርዓት ደካማ መሆኑን የመዲናዋ የደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ኤጀንሲ አስታወቀ። በኤጀንሲው የቆሻሻ መልሶ መጠቀም ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ፀጋዬ ይህን ያስታወቁት “በህብረተሰቡ የላቀ ተሳትፎ የመልካም ልማታዊ አስተዳደር ጉዟችን ግቡን ይመታል” በሚል ርእስ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባዘጋጁት የምክክር መድረክ ላይ ነው። የምክክር መድረኩ ለአራተኛ ጊዜ ሲሆን ከዚህ ቀደም በከተማው የቤቶች ልማት፣ በጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት እንቅስቃሴ፣ በመንገድና ውሃ ልማት እንደዚሁም በትምህርትና ጤና ላይ ያተኮሩ ውይይቶች የተካሂደዋል። በከተማው “የማህበረሰብ የልማት ተሳትፎ የቆሻሻ አወጋገድና መልሶ መጠቀም” ላይ ባተኮረው በዚህ መድረክ የመወያያ ሀሳብ ያቀረቡት አቶ ካሳሁን እንደተናገሩት፤ ቆሻሻ በማስወገድ ስርዓትና ወደ ኃብት መቀየር በሚቻልበት ስልት ዙሪያ የተወሰነ ለውጥ ቢኖርም አሁንም ሰፊ ድክመት አለ። የከተማዋን ቆሻሻ የማስወገድ ተግባር ዘመናዊ በሆነ መንገድ ማስተዳደር እንዲቻል የቆሻሻ ማስወገጃ ተሽከርካሪዎችን በማቅረብና በዘርፉ የተደራጁ የግል ማህበራትን ለማሰማራት ጥረቶች ተደርገዋል። አውቆ ማጥፋትን ጨምሮ በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በሚታየው የአመለካከት ችግር የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት እንዳላስቻለ ነው አቶ ካሳሁን የገለፁት። “የኤሌክትሪክ ኃይልና የባዮጋዝ ቴክኖሎጂን ጥቅም ላይ ለማዋል በሚደረገው ጥረት ቆሻሻ ግብኣት ከመሆኑ በተጨማሪ የኃብት ምንጭም ሊሆን ይችላል'' ብለዋል። በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ቆሻሻን የኃብት ምንጭ ለማድረግ በተከናወኑ ተግባራት ከ61 ሚሊዮን ብር ላይ ገቢ መገኘቱን ጠቁመዋል። ይህ ኃብት የተገኘውም 59 ቶን ቆሻሻን መልሶ መጠቀምን ጨምሮ ለተለያዩ ተግባራት ግብአት እንዲሆን በመደረጉ እንደሆነ ገልጸዋል። የውይይቱ ተሳታፊዎች በከተማዋ ያለውን ቆሻሻ በአግባቡ በማስተዳደር ረገድ ድክመቶች መኖራቸውን ነው የተናገሩት። በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 የፅዳት ማህበር ሰብሳቢ አቶ ዮናስ እሸቱ በየአካባቢው ይገነባሉ የተባሉት የቆሻሻ ማጠራቀሚያዎች እስካሁን ባለመገንባታቸው ከየቤቱ የሚወጣውን ቆሻሻ ጥንቃቄ በጎደለው መንገድ በየስፍራው የሚጣልበት ሁኔታ መቀጠሉን ገልፀዋል። በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 የልማት ዓብይ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አበበ ኃይሉ በበኩላቸው “የመዲናዋ የደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ኤጀንሲ አሰራሩን ዘመናዊ ለማድረግ እየሰራ ቢሆንም የቆሻሻ አሰባሰብ ችግርን መፍታት አልቻለም'' ብለዋል። ዘመናዊ ተሽከርካሪዎችን በመጠቀምና ቆሻሻ የሚያሰባስቡ ማህበራትን በማደራጀት የሚደረገው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የማህበራዊ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ጉዝጉዝ አበበ ናቸው። ሆኖም አሰራሩ ላይ ተገቢ በሆነ የክትትልና ቁጥጥር ስርዓት የታገዘ ባለመሆኑ ውጤታማ መሆን እንዳልቻለ ነው ወይዘሮ ጉዝጉን የተናገሩት። አቶ ካሳሁን ጸጋዬ ለተነሱት አስተያየቶች ማብራሪያ ሲሰጡ   የደረቅ በቆሻሻ አወጋገድና አስተዳደር  የሚታየውን የቅንጅት፣ የቁጥጥርና ክትትል ስርዓት ለማጠናከር ቃል ገብተዋል። የከተማውን የቆሻሻ አስተዳደር ለማዘመን ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን በቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ላይ በማህበረሱ ዘንድ ያለውን አመለካከት ለመቀየር፤ ቆሻሻን ለተለያዩ ግብአቶች በመጠቀም የኃብት ምንጭ የሚሆንበትን ስርዓት ለማጠናከረ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ ከዘርፉ ጋር በተያያዘ በወጡ ህጎች መሰረት አካባቢን በማያፀዱና ቆሻሻን በዘፈቀደ በሚጥሉ አካላት ላይ የሚወሰደው እርምጃም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል። በየአካባቢው ዘመናዊ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ለመትከል የተያዘው እቅድ እየተተገበረ መሆኑንም ጠቅሰዋል። የከተማዋ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ይስሃቅ ግርማይ እንደገለፁት፤ የመንግስት በጀት ውስን ቢሆንም የህብረተሰብ ተሳትፎ ከታከለበት በቆሻሻ አወጋገድና አስተዳደር ላይ ትልቅ ውጤት ማምጣት ይቻላል። ከተማው ፈርሶ እየተገነባ መሆኑን የሚገልፁት አቶ ይስሃቅ ከኢትዮጵያም የአፍሪካ ዋና ከተማ ብትሆንም በፅዳት ደረጃ ከአፍሪካ ከተሞች ብቻ ሳይሆን ከክልል ከተሞች ጋር ስትነፃፀርም ብዙ የሚቀራት እንደሆነች ተናግረዋል። በምክክር መድረኩ የተነሱትን ሀሳቦችና አስተያየቶች ተግባራዊ ለማድረግ የከተማ አስተዳደሩ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም