ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 3166 ደረሰ

ሰኔ 6/2012(ኢዜአ) በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓት በተደረገ 5644 የላቦራቶሪ ምርመራ ተጨማሪ 268 ሰዎች ኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸው ሲሆን እስካሁን ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 3166 መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታወቁ።

በቫይረሱ ምክንያት ተጨማሪ የ 8 ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን እስካሁን የ55 ሰዎች ህይወት አልፏል።

ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ከ 1 እስከ 90 ዓመት የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉ 177 ወንድና 91 ሴት ናቸው። ከነዚህ መካከል 267ቱ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ አንዱ የውጭ ሀገር ዜና ነው።

ቫይረሱ እንዳለባቸው የተረጋገጠ 232 ሰዎች ከአዲስ አበባ፣12 ሰዎች ከኦሮሚያ ክልል፣8 ሰዎች ከአማራ ክልል፣6 ሰዎች ከትግራይ ክልል፣ 5 ሰዎች ከሀረሪ ክልል፣ 2 ሰዎች ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል፣ 2 ሰዎች ከአፋር ክልል እንዲሁም 1 ሰው ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መሆናቸው ተገልጿል።

ትላንት 44 ሰዎች (28 ከአዲስ አበባ፣ 6 ከአማራ ክልል፣ 3 ከኦሮሚያ ክልል እና 3 ከሀረሪ ክልል) ከበሽታው ያገገሙ ሲሆን አጠቃላይ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 495 ሆኗል።
በአጠቃላይ ቫይረሱ ተገኝቶባቸው በለይቶ ህክምና ውስጥ ያሉ 2614 ሰዎች ሲሆኑ ከነዚህ መካከል 39ኙ በፀና የታመሙ መሆናቸውን ዶክተር ሊያ ገልጸዋል።

በህብረተሰብ ውስጥ ባለው የቫይረስ ስርጭት ምክንያት ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ከዕለት ዕለት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑም ተጠቅሷል።

የጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ኢንስቲትዩት በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸው ባለፈው ሰዎች የተሰማቸውን ሀዘን በመግለጽ ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን ተመኝተዋል።

በሀገሪቱ እስካሁን 176 ሺህ 504 የላቦራቶሪ ምርመራ ተከናውኗል።

በሌላ በኩል ሰኔ 4 ቀን 2012 ዓ.ም በተደረገ ዕለታዊ መግለጫ ቫይረሱ በምርመራ እንደተገኘባቸው ከተገለጹት ሰዎች መካከል 17ቱ ከዚህ በፊት ሪፖርት ተደርገው በህክምና ማዕከል ውስጥ ያሉና ለክትትል ምርመራ የተደረገላቸው መሆናቸውን በመግለጽ ጤና ሚኒስቴር ይቅርታ ጠይቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም