ቀጥታ፡

ሠራዊቱ ሕዝባዊ እሴትን በመላበሱ ውስብስብ ግዳጆችን ለመወጣት አይቸገርም --- ከፍተኛ መኮንኖች

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 6/ 2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሰላም ማስከበር ተልዕኮው ሕዝባዊነትን በመላበሱ ውስብስብ ግዳጆችን ለመወጣት እንዳስቻለው ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ ከፍተኛ መኮንኖች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሰላም ማስከበር የጀመረው በኮሪያ ሲሆን፤ ላለፉት 70 ዓመታት በአህጉርና ዓለም አቀፍ ደረጃዎች ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ ነው።

አሁን በደቡብ ሱዳን፣ሱዳንና በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ(አሚሶም) ጥላ ሥር ሰላም እያስከበረች ነው።

የኢትዮጵያ ሰላም ከጎረቤት አገሮችና ከዓለም ሰላም የሚለይ አይደለም የሚለው ደግሞ መርሁ ነው።

የሰላም ማስከበር ማዕከል ዋና ኃላፊ ሌተና ጄኔራል ደስታ አብቼ ለኢዜአ እንደተናገሩት ሠራዊቱ በሄደበት ቦታ ሁሉ ሕዝብን መሠረት አድርጎ ስለሚሰማራ ውጤታማ ነው።

"ሠራዊቱ አገር ውስጥ ሰላም ሲያስከብርና ግዳጅ ሲወጣ ከሕዝቡ ጋር ነው'' ያሉት ዋና ኃላፊው፣ መርሁ በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ወቅትም ይሰራል ብለዋል።

ሠራዊቱ በሌሎች አካባቢዎች ላይ ግዳጁን ሲወጣ ልክ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚያደርገው ከሕዝብ ጋር እየተመካከረና እንደ ራሱ ሕዝብ እያየ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም ሠራዊቱ የተገነባበት እሴት ነው ብለዋል።

እንደ ሌተና ጄኔራል ደስታ ገለጻ ሠራዊቱ ግዳጁን በሚገባ የሚወጣበት ሥልጠና ይሰጠዋል።

በዚህም ሠራዊቱ የሚሄድበት ቦታ ባህል፣አኗኗር፣የግዳጁ ምንነትና አፈጻጸምን አስመልክቶ ግንዛቤ እንዲጨብጡ ይደረጋል ብለዋል።

የ24ኛ ሞተራይዝድ ሻለቃ የአብዬ ዘማች አዛዥ ኮሎኔል መብራሃቶም ኃይሉ በበኩላቸው ሠራዊቱ ሰላም ለማስከር በሚገባባቸው ቦታዎች በተለይም በድንበር ጉዳዮች ገለልተኛነቱን ጠብቆ ስለሚሰራ ተመራጭ እንዳደረገው ይናገራሉ።

ሠራዊቱ ሕዝብን በቀለምና በኃይማኖት ሳይለይ በእኩልነት የማገልገል እሴቱ ተወዳጅ እንዳደረገው ይመሰክራሉ።

በተለይ አረጋውያን፣ህጻናት ፣ነፍሰጡሮችና ለአደጋ የተጋለጡ ሰዎችን ይታደጋል ብለዋል።ሠራዊቱ በሩዋንዳ፣ቡሩንዲ፣ላይቤሪያ፣ዳርፉር፣ በአብዬና በሶማሊያ ግዳጁን በስኬት እንዳከናወነ ኮሎኔል መብራሃቶም አስታውሰዋል።

ከሠራዊቱ የስምሪት ስኬቶች መካከል በደቡብ ሱዳንና ሱዳን መካከል በአብዬ ግዛት የተፈጠረውን አለመግባባት ገለልተኝነቱን ጠብቆ የፈታበት አንዱ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም