ቀጥታ፡

የአገር ደህንነትን ከማስጠበቅ ጎን ለጎን ራሳቸውን ከኮሮናቫይረስ እየጠበቁ መሆናቸውን የሠራዊት አባላት ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 06/2012 (ኢዜአ) የአገር ደህንነትን ከማስጠበቅ ጎን ለጎን ራሳቸውን ከኮሮናቫይረስ እየጠበቁ መሆናቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የመከላከያ ሠራዊት አባላት ገለጹ።

የኮሮናቫይረስ ከተከሰተ ጀምሮ በዓለም ላይ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ሲቀጥፍ ሚሊዮኖች ደግሞ በቫይረሱ ተይዘዋል።

ወረርሽኙ እየፈጠራቸው ያሉ የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውሶችና ዳፋዎችም በጋሃድ እየታዩ ናቸው።

በኢትዮጵያም ኮሮናቫይረስ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ 47 ሰዎች በቫይረሱ ሲሞቱ ወደ 3 ሺህ የሚጠጉ ዜጎች ደግሞ ተይዘዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ራሳቸውን ከቫይረሱ መጠበቅ ካልቻሉ አገርን የመጠበቅ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት እንደማይችሉ ተናግረዋል።

የዓለም ሥጋት የሆነውን ቫይረስ በኃላፊነት አለመከላከል የአገር ህልውናን አደጋ ውስጥ እንደሚከት ገልጸው ሠራዊቱ ራሱን እንዲጠብቅ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

ሻምበል ግዛቸው አበበ ሠራዊቱ ድርብ ኃላፊት ያለበት መሆኑን በመገንዘብ ራሳቸውን ከኮሮናቫይረስ እየተከላከሉ መሆናቸውን ገልጸው፣ በቀጣይም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው የተናገሩት።

ሀገርን ለመጠበቅና ሰላሟን ለማስከበር ቅድሚያ እራስን መጠበቅ ወሳኝ ነው ብላዋል።

ከሠራዊቱ አባላት በተጨማሪ ሌሎች ሲቪል ዜጎች በኮሮናቫይረስ እንዳይያዙ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ መሆኑንም አመልክተዋል። 

 በአካላዊ ርቀትና ንጽህና አጠባበቅ ላይ ከጤና ባለሙያዎችና ከሠራዊቱ የበላይ አመራሮች በኩል የግንዛቤ ማስጨበጫ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን የገለጹት ደግሞ መቶ አለቃ ልደት አስረስ ናቸው።


በሰራዊቱ መካከል ምንም አይነት መዘናጋት እንደለሌ ገልጸው ፣ ሰራዊቱ ወረርሽኑን ለከላከል የሚያደርገው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ወታደር ፍቅር መሀመድ ናቸው።

ለሰራዊቱ የበሽታው መከላከያ ቁሳቁሶች እንደተሰጣቸው ገልጸው፣ እራሳቸውንና ሀገራቸውን በመጠበቅ ላይ ነን ብላዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም