ቀጥታ፡

ቦርዱ የቀድሞ የኢሕአዴግ ንብረትን እንዲያጣሩ ሁለት ኦዲተሮችን ሾመ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 6/2012(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቀድሞ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ንብረት እንዲያጣሩ ሁለት ኦዲተሮች መሾሙን ገለፀ፡፡

ቦርዱ ጥር 20 ቀን 2012 ዓ.ም የአራት ድርጅቶች ስብስብ የሆነው ኢሕአዴግ እንዲፈርስ መወሰኑ ይታወቃል።

በመሆኑም የቀድሞው ብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን)፣የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ)፣የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) ወይም ሦስቱ/ የግንባሩ አባላት ወራሽ የሆነው በብልጽግና ፓርቲና በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በስድስት ወራት ውስጥ የንብረት ክፍፍል እንዲጠናቀቅ ትእዛዝ ሰጥቷል።

ክፍፍሉም የሶስት ፓርቲዎች ወራሽ የሆነውና በቦርዱ ሕጋዊ እውቅና ያገኘው ብልፅግና ፓርቲ የሃብቱን ሦስት አራተኛ (3/4) ፤ ህወሃት አንድ አራተኛ ( ¼) እንዲወስዱ መወሰኑ ይታወሳል፡፡

በውሳኔውም ፓርቲዎቹ የጋራ ንብረት አጣሪ ሾመው የባለመብቶችን (creditors) መብት እንዲጠበቅ እንዲሁም በተገለጸው ቀመር መሠረትም ክፍፍሉ እንዲፈጸም ወስኖ አሳውቆ ነበር፡፡

በሌላ በኩል የብልጽግና ፓርቲ የንብረት ክፍፍሉ እያንዳንዱ ፓርቲ በተናጠል በነበረው የአባላት ብዛት ላይ የተመሰረተ እንጂ፤ በእኩልነት ሊሆን አይገባም የሚል አቤቱታ አቅርቧል።

በመሆኑም ቦርዱ የሃብት ክፍፍሉን የወሰነው የፓርቲው ህገ ደንብ “ሁሉም ፓርቲዎች በግንባሩ የጋራ ንብረት እኩል የመጠቀም መብት አላቸው” ተብሎ በተቀመጠው መሠረት መሆኑን ገልጿል።

ነገር ግን የብልጽግና ፓርቲ ከዚህ የተለየ ውጤት የሚያስከትል ማስረጃ ወይም ሰነድ ካለው ለአጣሪው ማቅረብ እንደሚችል ተገልጾለታል።

የመፍረስ ውሳኔው ከተሰጠበት ጊዜ ጀምሮ ሁለቱም ወገኖች የሚስማሙበት አንድ የጋራ አጣሪ ለመምረጥ የተደረገው ጥረት አለመሳካቱን ቦርዱ አመልክቷል።

ስለሆነም ቦርዱ ብልጽግና ፓርቲና ህወሃት በየበኩላቸው የመረጧቸው አንድ አንድ የሂሳብ አጣሪዎች በጋራ ሆነው ንብረቱን እንዲያጣሩ ወስኗል፡፡

በዚህም ውሳኔ መሠረት የንብረት ማጣራቱን እንዲያደርጉ የተመረጡት ድርጅቶች የጋራ የሥራ ዕቅድ፣ የጊዜ ሰሌዳ፣ ሥራውን የሚያከናውኑበት ቦታ፣ ሁኔታና የሥራ ሕግጋት ለቦርዱ እንዲያቀርቡም በደብዳቤ መገለጹ ተጠቅሷል፡፡

የንብረት ማጣራቱ ሂደት ሙሉ ወጪ በፓርቲዎቹ የሚሸፈን ሲሆን፣ ቦርዱ ሂደቱ የሚደርስበትን ደረጃ በየጊዜው ለሕዝብ እንደሚያሳውቅ ዛሬ ቦርዱ በፌስ ቡክ ገጹ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም