ቀጥታ፡

ካውንስሉ ሕጋዊ ዕውቅና ማግኘቱ በተደራጀ መልክ ለመንቀሳቀስ ያስችላል አለ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 06/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ሕጋዊ ዕውቅና ማግኘቱ በተደራጀ መልክ ለመንቀሳቀስ እንደሚያስችለው ገለጸ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካውንስሉን ሕጋዊ ዕውቅና ለመስጠት የቀረበውን ረቂቅ ዓዋጅ ሰኔ 4 ቀን 2012 ዓ. ም በአብላጫ ድምፅ ማጽደቁ ይታወቃል።

የካውንስሉ ፕሬዚዳንት ዶክተር ኢያሱ ኤሊያስ በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት ካውንስሉ ሕጋዊ መብት ማግኘቱ የመብት ጥያቄዎች ለመጠየቅና የልማት ሥራዎችን ለማከናወን ያስችለዋል።

በቀጣይም በልማት ሥራዎች ላይ የሚያደርጉትን ተሳትፎ እንደሚያጠናክሩ አመልክተዋል።

መንግሥት ለዘመናት ለተጉላላው ጥያቄያቸው ፈጣን ምላሽ በመስጠቱ ፕሬዚዳንቱ ምስጋና አቅርበዋል።

የወንጌል አማኞች ቤተክርስቲያን ሕጋዊ ስላልነበር አማኞች እንግልትና ጫና ሲደርስባቸው መቆየቱን አስታውሰው፤በተለይም ጸሎት ቤቶች ሲቃጠሉና ወንጌላውያን ድብደባ ሲፈጸምባቸው እንደነበር ገልጸዋል።

የካውንስሉ ጠቅላይ ፀሐፊ ቄስ ደረጀ ጀምበሩ በበኩላቸው ''የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች ከሌሎች የሃይማኖት  ተቋማት ጋር የሚተባበር እንጂ፤ የሚወዳደር አይደለም'' ብለዋል።

በመሆኑም ከሌሎች የእምነት ተከታዮች ጋር ተባብሮ ለአገር አንድነት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በአገሪቷ በተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የተዘጉት ቤተ እምነቶች ተከፍተው በጋራ ማምለክ እስኪጀመር ምዕመናን በቤታቸው ሆነው እንዲጸልዩ አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ የወንጌል አማኞች ከሕዝቡ አንድ ሦስተኛ ያህል እንደሚሆኑ ይገመታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም