ቀጥታ፡

"እንደማመጥ" የመገናኛ ብዙሃንና ጋዜጠኞች የአደባባይ ቅስቀሳ መርሃግብር እንደቀጠለ ነው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 06/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋዜጠኞች በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ከተማ የኮሮናቫይረስ ስርጭት እየተስፋፋ በመጣበት አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ተገኝተው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ አከናውነዋል።

የመገናኛ ብዙሀን ሥራ ኃላፊዎችና ጋዜጠኞች ካለፈው ሰኔ 3 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎችና በክልል ከተሞች ለህብረተሰቡ ስለበሽታው ግንዛቤ እያስጨበጡ ይገኛሉ።

በዛሬው ዕለትም የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋዜጠኞች ወይዘሮ የሺመቤት ደመቀ እና አቶ አዋድ አብዱልባስጥ  በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ  በመገኘት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጥ መልዕክቶችን ለህብረተሰቡ አስተላልፈዋል።

በተቋሙ የዜና ክፍል ከፍተኛ አዘጋጅ የሆነችው ጋዜጠኛ የሺመቤት ደመቀ በዚህ ወቅት ህብረተሰቡ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ላይ ከፍተኛ መዘናጋት እንደሚታይበት መታዘቧን ተናግራለች።

በተለይ ህዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች፣ በገበያና በትራንስፖርት መናኽሪያዎች ሰዎች አካላዊ ርቀታቸውን ጠብቀው እየተንቀሳቀሱ አለመሆኑን ማየታቸውን ገልጸዋል።

ይህም የሰዎችን ለቫይረሱ የመጋለጥ አድል ስለሚያሰፋ ህብረተሰቡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወረርሽኙ እየተስፋፋ መምጣትን ግምት ውስጥ በማስገባት ከመቼውም ጊዜ በላይ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አስገንዝበዋል።

በድርጅቱ የውጭ ቋንቋዎች ምክትል ዋና አዘጋጅ አዋድ አብዱልባስጥ በበኩሉ "ኮሮናቫይረስን ለመከላከል ከመንግስት እና ከጤና ባለሙያዎች በየጊዜው የሚተላለፉ የመከላከያ መንገዶችን ህብረተሰቡ በአግባቡ ያለመተግበር ችግር ይታይበታል" ብሏል።

በህዝቡ ዘንድ የታየው መዘናጋት በአሁኑ ወቅት ዋጋ ማስከፈል መጀመሩን የገለጸው ጋዜጠኛ አዋድ ፣ "በቀጣይም ሁሉም ሰው ካልተጠነቀቀ እንደ አገር ከፍተኛ ዋጋ ሊከፈል ይችላል" ሲል ስጋቱ ገልጿል።

ህብረተሰቡ አገሪቱ ያላትን የኢኮኖሚ አቅም፣ የጤና ባለሙያዎች እጥረትና ያልጎለበተ የጤና ስርዐዓትን ከግምት በማስገባት የራሱን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስቧል።

"ህብረተሰቡን ለማንቃትና ለውጥ ለማምጣት በሚከናወኑ መሰል የቅስቀሳ ተግባራት ላይ የተለያዩ የሲቪል ማህበራትና የተለያዩ አደረጃጀቶች ሊያስቀጥሉ ይገባል" ብለዋል።

"እንደማመጥ" በሚል መሪ ሀሳብ ላለፉት ጥቂት ቀናት እየተካሄደ ያለው የመገናኛ ብዙሃን አመራሮችና  ጋዜጠኞች የጎዳና ላይ ቅስቀሳ መርሃግብር በዛሬው ዕለት ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም