ቀጥታ፡

“የኢትዮጵያ ሕዝብ በሀገሩ ሕልውናና ክብር ከመጡበት ሞት የማይፈራ ጀግና ሕዝብ መሆኑን አይደለም ግብጽ ዓለምም ያውቃል”... ጀነራል ብርሃኑ ጁላ

ሰኔ 6/2012(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሕዝብ በሀገሩ ሕልውናና ክብር ከመጡበት ሞት የማይፈራ ጀግና ሕዝብ መሆኑን አይደለም ግብጽ ዓለም እንደሚያውቀው የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጀነራል ብርሃኑ ጁላ አስታወቁ።

ጀነራል ብርሃኑ ጁላ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳመለከቱት ግብጾች ኢትዮጵያዊያን ጦርነት ከመጣ እንዴት ጦርነትን መሥራት እንደሚችሉ በሚገባ ያውቁታል።

"የኢትዮጵያ ሕዝብ በሀገሩ ሕልውናና ክብር ከመጡበት ሞት የማይፈራ ጀግና ሕዝብ መሆኑን አይደለችም ግብጽ ዓለም ያውቃል። በሀገሩ ጥቅምና ሕልውና የሚደራደር ኢትዮጵያዊ የለም።" ነው ያሉት።

የጦር መሣሪያ በገፍ መሰብሰብ ብቻ በጦርነት ውስጥ ለድል አያበቃም ያሉት ጄኔራል ብርሃኑ፤ በጦርነት ውስጥ ለድል የሚያበቁ ሳይንሳዊ የሆኑ የጦርነት መሰረታውያን የሚባሉ ሕጎች እንዳሉም ጠቁመዋል።

ጀነራል ብርሃኑ እንዳሉት "ለድል የሚያበቁት የመሰረታውያኑ ቁልፎች በሙሉ በኢትዮጵያውያን እጅ ናቸው፤ ግብጾች 30 እና 40 ዓመት ሙሉ የሰበሰቡት ብዙ አይነት የጦር መሣሪያ አላቸው፤ በዚህ አስፈራርተው የጋራ የሆነውን ውሃ እንዳትነኩ ለማለት ይሞክራሉ። መሪዎቿ በዚህ መልኩ ማሰብ አልነበረባቸውም።" ብለዋል።

ግብጻዊያን ከኢትዮጵያ ጋር በጭራሽ መጣላት ሳይሆን ኢትዮጵያዊያንን ተንከባክበው በመያዝ ውሃውን እንዴት አድርገን በጋራ እንጠቀም ማለት ነበረባቸው ያሉት ጀነራሉ፣ "ፈጣሪ ውሃውን ኢትዮጵያ ውስጥ ፈጠረው፤ ወደ ሱዳንና ግብጽ እንዲፈስ አደረገው፤ የወንዙ ውሃ ኢትዮጵያ፤ ሱዳን፤ ግብጽም ላይ ጥቅም ላይ ይውላል ብለዋል። ከዚህ ባለፈ ከላይ ያለው ሀገር እንጂ ከታች ያለው ሀገር ውሃውን መጠቀም አይችልም የሚለው እሳቤ አያስኬድም፣ የዓለም ሕግም አይደግፈውም፤ ይሄ የተሳሳተ የመሪዎቿ አስተሳሰብ ግብጽን በከፍተኛ ደረጃ ይጎዳታል" በማለትም ጠቁመዋል።

“ግብጽ አሁን የያዘችው መንገድ ለሀገሪቱ ብዙ ጠላት የሚያፈራባት ነው፤ ጠላትነት በጨመረ ቁጥር ጭራሹንም ውሃው ሙሉ በሙሉ የእኔ ነው ወደሚል የእልህ መንገድ ይወስዳል” ያሉት ምክትል ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹሙ፣ "መቼም ቢሆን የግብጽ ሠራዊት ኢትዮጵያ ገብቶ ምሽግ ሠርቶ የዓባይን ገባር ወንዞች አይጠብቅም፤ የኢትዮጵያን ምድርንም አይረግጥም፤ እነዚህ ወንዞቻችን ከጦርነትም በላይ ታላቅ አቅምና ጉልበት አላቸው" ብለዋል።

የግብጽ መሪዎች፤ ፖለቲከኞች ሚዲያቸውና ምሁራኑ የግብጽ ሕዝብ እንዲደነግጥ እንዲፈራ ውሃ የሚያጣ እንዲመስለው አድርገው ውሃ የምትለቅለትን ኢትዮጵያን በጠላትነት እንዲመለከት የረዥም ዘመን ሥራ ሠርተዋል ያሉት ጀነራሉ፣ ዛሬ ችግር ያመጣባቸው ይሄ ይመስለኛል ብለዋል።

የፖለቲካ አመራር ማለት የግብጽን ሕዝብ ዘላቂ ጥቅም አይቶ ሕዝብ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር በመከባበር በፍቅር በወንድማማችነት አስተሳስሮ ያለጦርነትና ያለጠላትነት በጋራ እንዲጠቀም ማድረግ ነው በማለት፤ ብልህና አርቆ አሳቢ ለሀገሩና ለህዝቡ የሚጨነቅ የፖለቲካ መሪ ማድረግ የሚጠበቅበት ይህንን ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የተሳሳተ የመሪዎቿ አስተሳሰብ ግብጽን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚጎዳትም አመልክተዋል።

"ጠላትን መቀነስ ወዳጅን ማብዛት የሚባል ስሌት አለ። መፎከር ሁሉም አማራጭ ጦርነትን ጨምሮ ጠረጴዛ ላይ ነው ያለው ማለት የሀሰት ሪፖርት ጽፎ መበተን፤ ግዙፍ የሚዲያ ዘመቻ ከፍቶ ኢትዮጵያን ማጥላላት በጠላትነት መፈረጅ ትርጉም የለሽ ነገር ነው" ብለዋል ጀነራል ብርሃኑ ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም