ቀጥታ፡

ህወሓት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ያቀረበው ጥሪ “ጩኸቴን ቀሙኝ ነው”... ዶ/ር አረጋዊ በርሄ

ሰኔ 6/2012 (ኢዜአ) ህወሓት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተለይም ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) እና ለአፍሪካ ኅብረት በኢትዮጵያ ላይ ያንዣበበውን አደጋ ለማስወገድ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ሲል ከሰሞኑ ያቀረበው ጥሪ “ጩኸቴን ቀሙኝ ካልሆነ በስተቀር እንዲህ ያለ ግፍ፤ አፈና እና ግድያ ያለው ህወሓት በመሸገበት ትግራይ ክልል ነው” ሲሉ ዶክተር አረጋዊ በርሄ ተናገሩ፡፡

ከዋልታ ቴሌቪዥን ፊትለፊት ፕሮግራም ጋር ቆይታ የነበራቸው የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ዶክተር አረጋዊ በርሄ ክሱ መሰረተቢስ እና ከእውነት የራቀ ውንጀላ ነው ሲሉ ገልጸውታል፡፡

ዶ/ር አረጋዊ አምባገነናዊ ስርዓት ያለው በትግራይ እንጂ እንደ ሀገር በዚህ ልክ የሚገለጽ የመንግስት ስርዓት የለም ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በኮቪድ-19 ሳቢያ መካሄድ ያልቻለው 6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ በመጨረሻም ወረርሽኙ የጤና ስጋት አለመሆኑን የጤና ሚኒስቴርና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ይፋ ካደረጉ በኃላ ከ9 ወራት እስከ አንድ አመት ባለ ጊዜ ውስጥ ተፈጻሚ እንዲሆን ውሳኔ ላይ ተደርሷል፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ መንግሥት ትርጉም እና የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ 6ኛውን ብሔራዊ ምርጫ ለማራዘም ያቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ በ4 ተቃውሞ፣ በአንድ ድምፀ-ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል።

ይሁን እንጂ የትግራይ ክልል መንግስት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተለይ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) እና የአፍሪካ ኅብረት በኢትዮጵያ ላይ ያንዣበበውን አደጋ ለማስወገድ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ሲል ጥሪ ማቅረቡ ይታወቃል፡፡

ዶ/ር አረጋዊ ይሄ ጥሪ ጩኸቴን ቀሙኝ ካልሆነ በስተቀር አሁን ያለው መንግስት የሐሳብ ልዩነትን የሚያስተናግድ ዴሞክራሲያ ሽግግር በማድረግ ላይ ያለ በመሆኑ ይህ አይነቱ ውንጀላ መሰረተ ቢስ ከመሆኑም በላይ ተቀባይነት የለውም ብለዋል፡፡

ኢሕአዴግን አፍርሶ በብልፅግና ፓርቲ የመተካቱ ሒደት ደም አፋሳሽ ያልሆነ የመንግሥት ግልበጣ ሊባል እንደሚችል በመግለጫው የተገለጸ ሲሆን፣ ‹‹እንደ ህወሓትና ሌሎች የፖለቲካ ተዋናዮች ብልሃት የተሞላበት አካሄድ ባይሆን ኖሮ እንዲህ ዓይነት ሕገወጥ የሥልጣን መቆናጠጥ ወደ ሕገ መንግሥታዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ሊያመራ ይችል ነበር፡፡›› ሲል ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ባቀረበው ባለ አሥር ገጽ አቤቱታ አስታውቋል፡፡

ዶ/ር አረጋዊ እነዚህ መገለጫዎች ያሉት አሁን በስራ ላይ ባለው መንግስት ሳይሆን በራሱ በህወሓት አስተዳደር ነው ይላሉ፡፡

ለዚህም ማሳያው ከሰሞኑ በክልሉ የተከሰቱ የወጣቶች ጥያቄና የክልሉ መንግስት የወሰደው ርምጃ መሆኑን አክለዋል፡፡

ከውሳኔው አስቀድሞ የምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባኤ የነበሩት ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም በፈቃዳቸው ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ይታወሳል፡፡

ወ/ሮ ኬሪያ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት የአገሪቱን "ሕገ መንግሥት በየቀኑ ከሚጥስና አምባገነንነትን ከሚያራምድ ቡድን ጋር ለመስራት ፈቃደኛ ስላልሆንኩና በስልጣን ላይ ያለው ወገን "ሕገ መንግሥቱን በግላጭ ጥሷል፤ አምባገነናዊ መንግሥት ወደ መመስረት ገብቷል" ሲሉ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

ይህን አስመልክቶ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ሊቀመንበር ዶ/ር አረጋዊ አቅም ያለው አመራር የልዩነቱን ሀሳብ ባገኘው መድረክና አጋጣሚ መታገልና የልዩነት ሀሳቡን ህዝቡ እንዲደግፈው ማድረግ ሲችል ሽሽት ተገቢ አይደለም ሲሉ የአፈ ጉባኤዋን መልቀቅ ተችተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም