ቀጥታ፡

የትግራይ ሕዝብ ድጋፍ ከተደረገለት ሕወሓትን ወደ ትክክለኛ መስመር መመለስ ካልሆነም ማክሰም እንደሚችል ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ6/2012(ኢዜአ) የትግራይ ሕዝብ ለውጥ ፈላጊ በመሆኑ ከኢትዮጵያዊያን ወገኖቹ ድጋፍ ከተደረገለት ሕወሓትን ወደ ትክክለኛ መስመር መመለስ ካልሆነም ማክሰም እንደሚችል አንድ የቀድሞ ከፍተኛ የሕወሐት አመራር ገለጹ።

የቀድሞ ከፍተኛ የሕወሓት አመራር አቶ ሚልዮን አብርሃ የትግራይ ሕዝብ በተለይ ወጣቱ ከአንድ አቅጣጫ ብቻ የሚሰነዘርንን አደገኛ ፕሮፓጋንዳ እየሰማ ከሰላምና ልማት ይልቅ አውዳሚ ጦርነት ናፋቂ እንዳይሆንም ጥሪ አቅርበዋል።

በድርጅቱ ስም እየተንቀሳቀሱ ያሉ ጥቂት ግለሰቦችም በክልሉ ውስጥ የሚነሳውን ተደጋጋሚ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ለማዘናጋትና ለማፈን እየሰሩ መሆኑን አቶ ሚሊዮን ለጀርመኑ ዶቼ ቬለ ገልጸዋል።

የትግራይ ሕዝብ ከጎረቤት ሀገርና ከሌላውም የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በነፃነትና በትብብር እንዳይሰራ እያደረጉት ይገኛሉ ሲሉም አቶ ሚሊዮን ወቅሰዋል።

በትግራይ የፖለቲካ ምኅዳሩ በክልሉ መንግሥት ተፅዕኖ ሥር በወደቁበትና በኮረና ወረርሽኝ ምክንያትተፎካካሪ ፓርቲዎች ዓላማና ፕሮግራማቸውን ማስተዋወቅ በማይችሉበት ቅቡልነት የሌለው ምርጫ አካሂዳለሁ ማለቱ ተገቢ አይደለም ሲሉም ተችተዋል።

እንኳንስ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሕወሓት አባላቶችም የሀሳብ ልዩነታችንን በነፃነት እንዳንገልጽ በአመራሩ የታፈነበት ሁኔታ መኖሩንም ገልጸዋል።

አቶ ሚሊዮን አያይዘውም ሕወሓትና የትግራይ ሕዝብ የተለያዩ መሆናቸው አፅንኦት ሊሰጠው ይገባልም ብለዋል።

በተለይም የፌደራል መንግሥት የሚመድብለትን ዓመታዊ በጀት የክልሉን ኢኮኖሚ ከመገንባት ይልቅ ለልዩ ሚሊሽያ ሥልጠናና ለወታደራዊ ቁሳቁሶች ግዢ እያባከነው መሆኑንም አቶ ሚሊዮን አስረድተዋል።

የክልሉ ሕዝብ ያሉበትን በርካታ የልማት፣ የመብት መከበርና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ከመፍታት ይልቅ አመራሩ በሀሳብ ልዩነት ሳይሆን በጭቅጭቅና በሹኩቻ ተጠምዷል ብለዋል።

የትግራይን ሕዝብ ከልማትና ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ወደኋላ እያስቀረና የሥልጣን ዕድሜውንም ለማርዘም የብሽሽቅ ፖለቲካን ዋና የመታጋያ ሥልቱ አድርጎ ሕዝቡ ሌሎች ወንድሞቹን እንዲጠላ እያደረገ ነው ብለዋል።

ድርጅቱ የክልሉ ሕዝብ የሚያነሳቸውን ተደጋጋሚ የልማት፣ የመብት መከበርና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለማዘናጋትና ለማፈን እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

የአንድ ፓርቲ አምልኮ እንዲኖር የትግራይን ሕዝብ ከጎረቤት ሀገርና ከሌላውም የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በሰላምና በፍቅር እንዳይኖር የግጭትና የጥላቻ አደገኛ ፕሮፓጋንዳን መንዛት የማታገያ ሥልቱ አድርጓል ሲሉም ወቅሰዋል።

ሕወሓት ከጥልቅ ተሃድሶው መድረክ በኋላም ልዩነቶችን በሰላማዊና በአሳማኝ ሁኔታ መፍታት እንዲሁም በሀሳብ ማሸነፍ የሚቻልበትን የፖለቲካ ምኅዳር አጥብቧል ብለዋል።

ሕወሐት ለሀሳብ ልዩነት ቦታ አለመስጠቱ፣ የተሻለ ሀሳብ ያለውን አመራር አለማስተናገዱና ዘመኑ ከሚፈልገው ለውጥ ጋር ለመሄድ ፍላጎት አለማሳየቱ ከአመራርነት በፈቃዳቸው ለመልቀቃቸው ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም