በፋይናንስ ዘርፉ የተደረጉ ማሻሻያዎች የግል ባንኮችን የገንዘብ ፍሰት እጥረት አስቀርቷል - ዳሽን ባንክ - ኢዜአ አማርኛ
በፋይናንስ ዘርፉ የተደረጉ ማሻሻያዎች የግል ባንኮችን የገንዘብ ፍሰት እጥረት አስቀርቷል - ዳሽን ባንክ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 06/2012 (ኢዜአ) መንግሥት በፋይናንስ ዘርፍ ያደረጋቸው ማሻሻያዎች የግል ባንኮች ሊገጥማቸው የሚችለውን የገንዘብ ፍሰት እጥረት ማስቀረቱን የዳሽን ባንክ ዋና ሥራአስፈፃሚ ገለጹ።
ኮቪድ-19 በዘርፉ ላይ የሚያደርሰውን ጫና ለመቋቋም ተቋማት ራሳቸውን ከሁኔታዎች ጋር ማላመድ አለባቸውም ብለዋል።
በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መግባቱ ከታወቀበት ቀን ጀምሮ የፋይናንስ ዘርፍ ችግር እንዳይገጥማቸው የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ሲደረጉ ቆይተዋል።
መንግሥት የግል ባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት እንዳይገጥማቸው ከወረርሽኙ በኋላ 48 ቢሊዮን ብር ገንዘብ ፈሰስ አድርጎላቸዋል።
ገንዘብ ሲያበድሩ ይገዙት የነበረው 27 በመቶ ቦንድ እንዲቀር ተደርጓል። ከቦንድ ግዥ የተከማቸው ገንዘብም ወደ ባንኮች ተመልሷል።
የንግድ ተቋማት ግብር ባለመክፈል፤ በቅጣትና በወለድ ምክንያት የተከማቸ ከ78 ቢሊዮን ብር በላይ ዕዳ ተሰርዟላቸዋል።
የዳሽን ባንክ ዋና ሥራአስፈፃሚ አቶ አስፋው ዓለሙ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በግብር መክፈያው ተመሳሳይ ወቅት መከሰቱ የግል ባንኮችን ፈትኗቸው ነበር።
በመሆኑም መንግሥት በኢኮኖሚው ላይ ያደረጋቸው ማሻሻያዎች ዘርፉ ሊገጥመው ከሚችለው የገንዘብ እጥረት አውጥቶታል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የፋይናንስ ዘርፉን ለማጎልበት የሚያወጧቸው ደንቦችና መመሪያዎችን የግል ባንኮች ተከታትለው ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
የፋይናንስ ተቋማትን አቅም ለማሳደግ የሚደረጉ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችም የአጭርና ረጅም ጊዜ መፍትሄዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ኮቪድ-19 በፋይናንስ ዘርፉ ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመቋቋም ተቋማት ራሳቸውን ከሁኔታዎች ጋር ማላመድ እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
ወረርሽኙ በኢኮኖሚው ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመቀነስ የመከላከያና መቆጣጠሪያ መንገዶችን ከህይወታችን ጋር ማዋሀድ አለብን ብለዋል።
ኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የግል ባንኮች ከ100 ሚሊዮን በላይ የገንዘብና ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸውን የገለጹት አቶ አስፋው፤ በቀጣይም ችግሩ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ ለመቆጣጠር መተባበርና መተጋገዝ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።