ቤተክርስቲያኗ ለጤና ተቋማትና ለተቸገሩ ወገኖች ድጋፍ አደረገች - ኢዜአ አማርኛ
ቤተክርስቲያኗ ለጤና ተቋማትና ለተቸገሩ ወገኖች ድጋፍ አደረገች
ዲላ፣ ሰኔ 06/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጱያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ደቡብ ሲኖዶስ በኮቾሬ ወረዳ ለጤና ተቋማትና በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ለችግር ለተጋለጡ 96 ወገኖች የገንዘብና ንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገች።
በቤተክርስቲያኗ የልማትና ማህበራዊ አገልግሎት ኮሚሽን የደቡብ ሲኖዶስ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ ተድላ አረጋ ድጋፉን ትናንት ለወረዳው የኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ ኃይል አስረክበዋል።
በዚህ ወቅት ዳይሬክተሩ እንደገለጹት ድጋፉ በወረዳው ለሚገኙ ጤና ተቋማት የሚሆን 39 ካርቶን ሳሙና፣ 210 ብልቃጥ ሳኒታይዘር፣ 60 ሊትር አልኮልና የእጅ ጓንት ያካተተ ነው።
ቤተክርስቲያኗ በተጨማሪም በቫይረሱ ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ 96 ወገኖች በነፍስ ወከፍ 1 ሺህ 100 ብር ድጋፍ አድርጋለች።
ለድጋፉ ከ400 ሺህ ብር በላይ ወጪ መሆኑን ያመለከቱት ዳይሬክተሩ በቀጣይም እገዛው በሌሎች አከባቢዎች እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
በወረዳው ኮሮናን ለመከላከል ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ለማስጨበጥ እየተሰራ ቢሆንም የግብዓት ውስንነት እንቅስቃሴውን አስቸጋሪ እንዳደረገው የገለጹት ደግሞ የቫይረሱ መከላከል ግብረ ኃይል አባልና የኮቾሬ ወረዳ ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ታደሰ ናቸው።
ቤተክርስቲያኗ ያደረገችው ድጋፍ ችግሩን ለማቃለል እንደሚያግዝ ተናግሯል።
የገንዘብ ድጋፉ በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ለችግር የተጋለጡ ዜጎች ለከፋ ጉዳት እንዳይጋለጡ የሚፈልጉትን ከአቅራቢያቸው ገዝተው እንዲጠቀሙ የሚያስችላቸው መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የኮቾሬ ወረዳ ዋና አስተዳደሪ አቶ ብርሃኑ ማሞ ናቸው።
ቤተ ክርስቲያኗ ላደረገችው ድጋፍ ምስጋና አቅርበው በድጋፍ የተገኙ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለጤና ተቋማት እንደሚያሰራጩ አስታውቀዋል።
የቤተክርስቲያኗ ደቡብ ሲኖዶስ ፕሬዝደንት ቄስ ወልዴ አየለ በበኩላቸው ቤተ ክርስቲያኗ በአካባቢው ከምትሰጠው መንፈሳዊ አገልግሎት በተጓዳኝ የተለያየ ልማትና ሰላም ግንባታ ስራዎችን እያከናወነች መሆኑን ተናግረዋል።
"በዚህም አስቸጋሪ ወቅት ከወገን ጎን መቆም ያስፈልጋል " ያሉት ቄስ ወልዴ በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ለችግር እንዳይጋለጡ በማሰብ ቤተክርስቲያኗ ድጋፍ ማድረጓን ገልጸዋል።