የኮሮና ተጋላጭ በሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ ለመቋቋም የሚያግዙ የድጋፍ ስምምነቶች ተደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
የኮሮና ተጋላጭ በሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ ለመቋቋም የሚያግዙ የድጋፍ ስምምነቶች ተደረጉ
አዲስ አበባ ሰኔ 5/2012(ኢዜአ) የኮሮናቫይረስ ተጋላጭ በሆኑ የኅብረተሰበ ክፍሎች ላይ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ ለመቋቋም የሚያግዙ ሁለት የድጋፍ ስምምነቶች ተደረጉ።
ከስዊድን መንግስት በተደረገ የገንዘብ ድጋፍ የ116 ሚሊዮን ብር ስምምነት በዓለም አቀፍ የሕፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) በኩል ለስድስት ወር የሚተገበርና የልማታዊ ሴፍቲኔት ተጠቃሚዎች ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ እንዲያገኙ የሚያደርግ ነው።
ነብሰ-ጡርና የሚያጠቡ እናቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ በአለም የምግብ ፕሮግራም የሚደገፍ 20 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የድጋፍ ስምምነትም በተመሳሳይ በዛሬው እለት ተደርጓል።
የ116 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ስምምነቱ 49 ሺህ ቋሚ የቀጥታ ድጋፍ ተጠቃሚዎችን እንዲሁም 10 ሺህ ያህል ጊዜያዊ ድጋፍ ተጠቃሚዎች የኮሮናቫይረስ የሚያደርስባቸውን ተፅዕኖ ለመቀነስ የሚውል ነው።
ስምምነቱን የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፣ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ፣ የዩኒሴፍ የኢትዮጵያ ተወካይ ሚስ አዲል ኮዲርና በኢትዮጵያ የስዊድን አምባሳደር ቶርብጆርን ፒተርሰን ተፈራርመዋል።
ድጋፉ በ11ዱ የከተማ ሴፍቲኔት ተጠቃሚ ከተሞች የሚሰጥ መሆኑ ተገልጿል።
በዚህ ወቅት የዩኒሴፍ የኢትዮጵያ ተወካይ ሚስ አዲል ኮዲር እንዳሉት፤ የኮሮናቫይረስ ተጋላጭ በሆኑ ህፃናትና የተለያዩ የኀብረተሰብ ክፍሎች ላይ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ ለመቀነስ የኢትዮጵያ መንግስት እየወሰደ ያለው የማህበራዊ ጥበቃ እርምጃዎች የሚበረታታና ለቀጣናው አገሮች ተምሳሌት የሚሆን ነው።
''ዩኒሴፍ ይህን የመንግሥት ተግባር ይደግፋል፤ በተለይም ለህፃናት፣ አጥቢና ነብሰ-ጡር እናቶች እንዲሁም ለአካል ጉዳተኞች ለሚደረገው ድጋፍ እገዛ ያደርጋል'' ብለዋል።
የስዊድን ህዝብና መንግሥት ላደረጉት አስተዋፅኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ድጋፉ ተጠቃሚዎቹ ለምግብና መድኃኒት መግዣ እንዲሁም ለሌሎች ወሳኝ ነገሮች የሚጠቀሙት ተጨማሪ ገንዘብ እንዲያገኙ ያስችላልም ነው ያሉት።
በተጨማሪም 17 ሺህ ነብሰ-ጡርና የሚያጠቡ እናቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ 20 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የድጋፍ ስምምነት በአለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ተወካይ ዶክተር ስቴቨን ዌር፣ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ ተፈራርመዋል።
''ስምምነቱ ድጋፍ የሚሹ ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለመድረስ ያስችላል'' ያሉት የአለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ተወካይ ዶክተር ስቴቨን ዌር ናቸው።
የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንደገለጹት፤ ስምምነቶቹ እነዚህን የማህበረሰብ ክፍሎች ከኮሮናቫይረስ ለመከላከልና የሚደርስባቸውን ጫና ለመቀነስ ይረዳል።
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ በበኩላቸው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ ለመቀነስ በ16 ከተሞች የሚገኙ የደሃ ደሃ ዜጎችን በመለየት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።