ቀጥታ፡

በምስራቅ ሐረርጌ ዞን 367 አሽከርካሪዎችንና ንግድ ተቋማት ተቀጡ

ሐረር ፣ሰኔ 5/2012 (ኢዜአ ) በምስራቅ ሐረርጌ ዞን የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የወጣውን አዋጅ ክልከላዎችን ተላልፈው ተገኝተዋል የተባሉ 367 አሽከርካሪዎችንና ንግድ ተቋማት በገንዘብ መቀጣታቸውን ፖሊስ አስታወቀ።

የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አባል የሆነው የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የኮሙዩኒኬሽን ዲቪዥን ተጠባባቂ ኃላፊ ኢንስፔክተር ቶሎሳ ጎሹ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት የተቀጡት አሽከርካሪዎችና ንግድ ተቋማት  በዞኑ  የተለያዩ ወረዳዎችና  ከተማ አስተዳደሮች የሚገኙ ናቸው።

አሽከርካሪዎቹ ከተፈቀደላቸው የተሳፋሪ ቁጥር በላይ ሰዎችን በመጫን እንዲሁም ከታሪፍ በላይ ክፍያ በማስከፈልና ለህዝብ ባልተፈቀደ ተሽከርካሪዎች ሰው ጭነው መገኘታቸውን ጠቅሰዋል።

በዚህም ጥፋት 348  አሽከርካሪዎች እያንዳንዳቸው ከ2 ሺህ እስከ 5 ሺህ ብር  መቀጣታቸውን ኢንስፔክተሩ ተናግረዋል።

ሌላው አለአግባብ በሸቀጦች ላይ  የዋጋ ጭማሪ አድረገው  የተገኙ 19 የንግድ ድርጅቶች  ከ15 እስከ 30 ሺህ ብር እንዲቀጡ መደረጉንም አስታውቀዋል።

በዞኑ በተለይ አካላዊ ርቀትን በማይጠብቁ ፣ተራርቀው ግብይት በማይፈጽሙ፣ በሸቀጦች ላይ የዋጋ ንረት በሚፈጥሩና ሌሎችንም የአዋጁን ክልከላዎች ጥሰው በሚገኙት ላይ እርምጃው  ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ኢንስፔክተር ቶሎሳ  አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም