ዜጎችን ከኮሮናቫይረስ ስርጭት መታደግ የመንግስት ወቅታዊ ቁልፍ አጀንዳ ነው - አቶ ንጉሱ ጥላሁን - ኢዜአ አማርኛ
ዜጎችን ከኮሮናቫይረስ ስርጭት መታደግ የመንግስት ወቅታዊ ቁልፍ አጀንዳ ነው - አቶ ንጉሱ ጥላሁን

አዲስ አበባ ሰኔ 5/2012(ኢዜአ) "የመንግስት ዋነኛ ትኩረት የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ በመሆኑ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን መግታት ቁልፍ አጀንዳችን ነው" ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ተናገሩ።
በደቡብ ክልል የተነሱትን የአደረጃጀት ጥያቄዎችን ለመፍታት ረዥም ርቀት የተጓዙ አሳታፊ ውይይቶች መደረጋቸውንም ገልጸዋል።
ሃላፊው ወቅታዊ አገራዊ ሁኔታዎችን በሚመለከት ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
የኮሮናቫይረስ በኢትዮጵያ በተከሰተባቸው የመጀመሪያዎቹ ጊዜያት ህዝቡ ጥብቅ ጥንቃቄ እያደረገ እንደነበር አስታውሰዋል።
''አሁን ላይ የቫይረሱ ስርጭት እየሰፋ ቢሆንም ህብረተሰቡ ስርጭቱን የሚመጥን ጥንቃቄ በማድረግ ረገድ መዘናጋት ይታይበታል'' ብለዋል።
በተለይ ከግንቦት ወር ወዲህ ባሉት ቀናቶች እጅግ አስደንጋጭ ጉዳቶች እየተመዘገቡ መሆኑንም ነው የገለጹት።
የዜጎችን ደህንነት ማረጋገጥ የለውጡ ዋነኛ ትኩረት መሆኑን ያስታወሱት ሃላፊው፤ በመሆኑን መንግስት የኮሮናቫይረስን ስርጭትን መግታት ወቅታዊ ቁልፍ አጀንዳው አድርጎ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በመንግስት የሚከናወኑ ተግባራት ብቻ የሚፈለገውን ለውጥ ስለማያመጡ ህብረተሰቡ የጥንቃቄ ምክረ ሃሰቦችን ሳይዘናጋ እንዲተገብርም ጥሪ አቅርበዋል።
በሌላ በኩል በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል በርካታ የአደረጃጀት ጥያቄዎች መቅረባቸውን ያነሱት አቶ ንጉሱ፤ ጥያቄዎቹ በሰላም እንዲፈቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር ህዝባዊ ውይይት ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።
በአደረጃጀት ጥያቄ ስም በሚነሱ ግጭቶች ክልሉ ያሉትን ጸጋዎች እንዳይጠቀም መደረጉን ጠቅሰው፤ ''ጥያቄዎችን በሰላም ለመፍታት የሚያስችሉ በርካታ ስኬታማ ምክክሮች ተደርገዋል'' ብለዋል።
ጉዳዩን በሚመለከት የሚደረጉ ያልተገቡ እንቅስቃሴዎች ቂምና ቁርሾን ለመጪው ትውልድ ከማትረፍ የዘለለ ሚና እንደሌላቸውም ተናግረዋል።
''በየትኛውም አስተዳደራዊ አደረጃጀት ውስጥ ብንሆንም ዘወትር ማሰብ ያለብን አብሮነታችንን ነው'' ብለዋል።
እስካሁን ባለው ሂደትም በክልሉ የተቋቋመ የምሁራን ኮሜቴና በፌደራል ደረጃ የተቋቋመው የሰላም አምባሳደሮች ኮሚቴ በጋራ በመሆን አሳታፊ ምክክሮችን ያደረገ መሆኑንም አብራርተዋል።
በቅርቡም የሰላም ሚኒስቴርን ጨምሮ ሌሎች የሚኒስቴር ተቋማትን ያቀፈ ኮሜቴ ተቋቁሞ በስራው ላይ እየተሳተፈ መሆኑንም አቶ ንጉሱ ጨምረው ገልጸዋል።