ቀጥታ፡

የመገናኛ ብዙሃን የኮቪድ-19 መከላከል ቅስቀሳ መርሃ ግብር እንደቀጠለ ነው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5/2012 (ኢዜአ)  የመገናኛ ብዙሃን አመራሮችና ባለሙያዎች የኮሮና ቫይረስ መከላከል ላይ ያተኮረ የአደባባይ ላይ ቅስቀሳ መርሃ ግብር ዛሬም ቀጥሏል።

"እንደማመጥ" የሚል መሪ ሀሳብ የያዘው የመገናኛ ብዙሃኑ የቅስቀሳ መርሃግብር የተጀመረው ከትናንት በስቲያ ነው።

በሁለቱ ቀናት የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን አመራሮች በተለያዩ አካባቢዎች በመዟዟር ግንዛቤ የመፍጠር ተግባር ያከናወኑ ሲሆን ዛሬም የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ቅስቀሳውን ቀጥለው ውለዋል።

በዚሁ መሰረት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ባለሙያዎች በአራዳ ክፍለ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች በመዟዟር የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን የተመለከቱ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል።

በተቋሙ የዘጋቢ ፊልም ምክትል ዋና አዘጋጅ አለምጸሐይ መክቴ ያልተገባ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎች አወጋገድ ለቫይረሱ መስፋፋት መንስኤ በመሆኑ ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስባለች።

ቫይረሱን መከላከል ከራስ እንደሚጀምርና ራስን መጠበቅ የሌሎችንም ህይወት መታደግ በመሆኑ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ሃላፊነት መወጣት አለበት ብላለች።

የዜና አዘጋጁ ኃይለየሱስ ተፈራ በበኩሉ መንግስት ሰዎች በቤታቸው እንዲቆዩ የወሰዳቸውን እርምጃዎች ተግባራዊ ያለማድረግ ሁኔታዎች ይስተዋላሉ ይህ ሊታረም ይገባል ብሏል።

ማኅበረሰቡ መንግስት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከለከል የሚያወጣቸውን መመሪያዎች ሳይሸራርፍ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባውም ገልጿል።

በወረርሽኙ ምክንያት ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጫና የደረሰባቸውን ዜጎች በመደገፍ ሕዝቡ የአብሮነት ባሕሉን ሊያሳይ እንደሚገባም ተናግሯል።

በ "እንደማመጥ" የመገናኛ ብዙሃንና የጋዜጠኞች የቅስቀሳ መርሃ ግብር የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ የዋልታ ቴሌቪዥን፣ የአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ፣ የአማራ መገናኛ ብዙሃን ድርጅት፣ የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔት ወርክና የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ባለሙያዎች ዛሬ በተለያዩ ስፍራዎች ቅስቀሳ አድርገዋል።

የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎቹ በነገው ዕለት በተለያዩ ስፍራዎች በኮቪድ-19 መከላከል ዙሪያ ቅስቀሳ የሚያደርጉ ሲሆን የመርሃ ግብሩም ማጠቃለያ ይሆናል።

የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የስራ ኃላፊዎችና ጋዜጠኞች በአዲስ አበባ፣ በባህርዳር፣ በአዳማና ሐዋሳ ከተሞች ቫይረሱን አስመልክቶ ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ መፍጠር የመርሃ ግብሩ ዓላማ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም