ቀጥታ፡

የመተንፈሻ ቀዳዳ የተገጠመላቸው የፊት መሸፈኛ ጭምብሎች ኮሮናቫይረስን ከመከላከል ጥቅማቸው ጉዳታቸው ያመዝናል

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5/2012 (ኢዜአ) የመተንፈሻ ቀዳዳ የተገጠመላቸው ጭምብሎች /ማስኮች/ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው ያመዝናል ሲል የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ ኮሮናቫይረስን መከላከል የሚያስችሉ የጭምብል /ማስክ/ አጠቃቀሞችን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

የባለስልጣኑ የመድኃኒትና የሕክምና መሳሪያዎች ምዝገባና ፈቃድ ዳይሬክተር አቶ አብደላ ቃሶ፣ ምን አይነት የፊት መሸፈኛ የት ቦታ፣ በምን አይነት አግባብ መጠቀምና ማስወገድ አለብን የሚለውን መመሪያ በመተግበር በሽታው የከፋ ጉዳት ሳያስከትል በመተጋገዝ መሻገር ይገባናል ብለዋል።

የኮሮና ቫይረስን ከመከላከል ይልቅ ጉዳታቸው ያመዝናል ስለተባሉት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎችም ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የመተንፈሻ ቀዳዳ የተገጠመላቸው ጭምብሎች /ማስኮች/ በቀዳዳው የሚወጣው ትንፋሽ በቀጥታ በአካባቢው ለሚገኝ ሰውና ቁስ ስለሚለቀቅ መሰል ጭምብሎችን ባለማድረግ የቫይረሱን ስርጭት መከላከል ይገባል ነው ያሉት።

አቶ አብደላ ቫይረሱን መከላከል የሚያስችሉ ግብዓቶችን በአገር ውስጥ ማምረት እንዲቻል እየተሰሩ ያሉ ስራዎችንም አብራርተዋል።

የአገር ውስጥ መድሃኒት አምራቾች ሳኒታይዘር ማምረት የሚያስችል ጊዜያዊ ፈቃድ አውጥተው ወደ ስራ መግባታቸው ያለውን እጥረትና ከውጭ ለማስገባት የነበረውን ውጣ ውረድ ማቅለሉንም ተናግረዋል።

ባለስልጣኑ በመደበኛነት ሲጠቀምባቸው የነበሩ ህጎች፣ ደንቦችና አሰራሮችን ከተገቢነታቸው አንፃር በማሻሻል ወረርሽኙን ለመከላከልና መቆጣጠር እየሰራ እንደሆነም ገልጸዋል።

መስሪያ ቤቱ ያለበትን የኅብረተሰቡን ጤና የመጠበቅ ኃላፊነት ከህግ አስከባሪና ሌሎች አካላት ጋር በመሆን በህገ-ወጥ መልኩ እየተሸጡ ያሉ የፊት መሸፈኛ ጭምብሎችና ሌሎች መድኃኒቶችን ለመቆጣጠር ጥረት እያደረገ ስለመሆኑም አስረድተዋል።

የባለስልጣኑ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ አበራ ደነቀ በበኩላቸው ‘’አስመጪዎች ወደ  መስሪያ ቤቱ መጥተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የወጡ ጊዜያዊ መመሪያዎችን መሰረት በማድረግ እየሰሩ መሆናቸውን’ ገልጸዋል።

የተለያዩ መጠን ያላቸው ቀዳዳ አልባ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎች በአምራችና እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች፣ በንግድ ተቋማትና ግለሰቦችም ጭምር ወደ አገር እንዲገቡ በማድረግ ጥቅም ላይ እንዲውሉ እየተደረገ ስለመሆኑ ተገልጿል።

ቬንትሌተር በአገር ውስጥ ለማምረት ፍላጎት ያላቸው ድርጅቶችም የወጣውን ጊዜያዊ መመሪያ በመከተል ወደ ስራ መግባት እንደሚችሉም ጥሪ ቀርቧል።

ባሕላዊ መድኃኒቶችን ለማምረትም የሕክምና ሙከራ መመሪያ መዘጋጀቱም ተገልጿል።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል፣ ለመመርመርና ለማከም ጥቅም ላይ የሚውሉ ግብዓቶችም ሆኑ የሕክምና ሙከራዎች ፈቃድ ካገኙ በኋላም ክትትልና ቁጥጥር እያደረገ መሆኑም ተነግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም