ቀጥታ፡

የሕዳሴው ግድብ የሕልውናችን ጉዳይ በመሆኑ ከዳር ማድረስ ግዴታችን ነው - የአ/አበባ ብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5/2012 (ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሕልውናችን ጉዳይ በመሆኑ ከዳር ማድረስ ግዴታችን ነው ሲል የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ አስታወቀ።

ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ግንባታን በማፋጠን ላይ ስትሆን ከመጪው ሐምሌ ጀምሮ የተወሰነ ውሃ ለመያዝ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑ ይታወቃል።

ዜጎች ግድቡ አሁን የደረሰበትን ቁመና እስኪላበስ ድረስ በቡድንና በተናጠል በ''የእኔነት'' ስሜት ካላቸው ሃብት በማካፈል ለግድቡ እውን መሆን እየተጉ ይገኛሉ።

የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ፕሬዚዳንት ወጣት አዕምሮ አዱኛ ለኢዜአ እንደገለፀው ግድቡ ኢትዮጵያዊያን ከድህነት ለመውጣት የሚያደርጉትን ትንቅንቅ በድል እውን የሚያደርጉበት ነው።

ኢትዮጵያ በዓባይ ያላትን ፍትሃዊ የውሃ ሀብት አጠቃቀም መብቷን ለዘመናት ተነፍጋ የቆየች ሲሆን ዛሬም ፕሮጀክቱን ለማሰናከል የተለያዩ የዲፕሎማሲ ጫናና ፕሮፖጋንዳ ይነዛል ብሏል።

ግድቡ የዜጎች የሕልውና ጉዳይ በመሆኑ፣ የወጣት ሊጉ የተለያዩ ድጋፎችን ሲያሰባሰብ መቆየቱን ነው የገለጸው።

ባለፉት 3 ወራት ብቻ 450 ሺህ ብር የቦንድ ግዥ እና 143 ሺህ ብር በጥሬ ማሰባሰብ ተችሏል።

በርካታ ኢትዮጵያዊያን እናቶች ምግብ ለማብሰል በጭስ እየተቸገሩ ዘመናት መሻገራቸውን በማስታወስ ''ድህነትን ለማባረር እንደ ዋነኛ ተስፋ የተያዘውን ፕሮጀክት የፖለቲካና ሌሎች ልዩነቶች ሳይገድቡን ማስቀጠል ግድ የሚለን ጊዜ ላይ ነን'' ብሏል ወጣት አዕምሮ።

የወጣት ሊጉ የግድቡን ግንባታ ከዳር ለማድረስ ወጣቶችን በማስተባበር እየተሰራ መሆኑን የገለጸው ደግሞ የሊጉ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወጣት በቀለ ታጀበ ነው።

"ይህ ወቅት የድላችን ዋዜማ በመሆኑ ሁሉም በእልህና በወኔ በቻለው ሁሉ የሕዳሴ ግድቡን ለማገዝ ርብርብ ይሻል" ብሏል።

የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን ሽታ በበኩላቸው በወረዳው አመራር አባላት የ200 ሺህ ብር ቦንድ ግዢ መፈጸሙን አንስተዋል።

ሕዝቡም የአቅሙን እንዲያደርግ የማስተባበር ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አንስተው፣ እስከ ሰኔ አጋማሽ ድረስ የ5 ሚሊዮን ብር የቦንድ ግዢ ለመፈጸም እየተሰራ መሆኑን አክለዋል።

ወጣቶቹም ግድቡ ተገንብቶ እስኪጠናቀቅ የማስተባበርና ገቢ የማሰባሰብ ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌትና አለቃቀቅ አስመልክቶ በኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ መካከል የሚደረገው የሶስትዮሽ ድርድር በየአገራቱ የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች በመካሄድ ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም