ቀጥታ፡

ለኢትዮ-ሱዳን የባቡር ፕሮጀክት የአዋጭነት ጥናት 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ፀደቀ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 5/2012(ኢዜአ) የአፍሪካ ልማት ባንክና ለአፍሪካ ልማት አዲስ አጋርነት የመሰረተ ልማት ፕሮጀክት ዝግጅት ፋሲሊቲ /ኔፓድ/ ለኢትዮ-ሱዳን የባቡር ፕሮጀክት የአዋጭነት ጥናት 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አፀደቁ።

ለአዋጭነት ጥናቱ ከሚያስፈልገው ገንዘብ ውስጥ ከአፍሪካ ልማት ባንክ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር ከኔፓድ ደግሞ 2 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ መገኘቱን የገለጸው የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ነው።

አዲስ አበባን ከፖርት ሱዳን የሚያገናኘው ይህ የባቡር ፕሮጀክት እንዲገነባ እ.ኤ.አ 2018 በሁለቱ አገራት መንግስታት የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ ላይ ነው ስምምነትቱ የተፈረመው።

የባቡር መስመሩ በኢትዮጵያ አዲስ አበባ፣ ወልድያ፣ ወረታ፣ ጐንደርና መተማን የሚያካልል ሲሆን በሱዳን በኩል ጋላባት፣ ጋዳሊፍ እና ፖርት ሱዳንን ይሸፍናል።

1 ሺህ 512 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ይህ መስመር 594 ኪ.ሜ የሚሸፍነው በኢትዮጵያ፤ ቀሪው 918 ኪሎ ሜትር ደግሞ በሱዳን ክልል ውስጥ ይሆናል።

12 ወራት የሚፈጀው የአዋጭነት ጥናት የባቡር ፕሮጀክቱን ቴክኒካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ አካባቢያዊ ተስማሚነትና አማራጭ የፋይንስ ዝግጅት የሚዳስስ ነው።

የአዋጭነት ጥናቱን ለማጥናት ያሸነፈው ሲ.ፒ.ሲ.ኤስ ትራንስኮም ሊሚትድ የተሰኘ የካናዳ አማካሪ ድርጅት ነው።

የባቡር መስመሩ ሲገነባ ኢትዮጵያን ከምስራቅ አፍሪካ አገራት ጋር በባቡር መሠረተ ልማት የሚያስተሳስር እንደሆነም ኮርፖሬሽኑ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም