የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ አባላት ችግኝ ተከሉ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5/2012 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ''ዛፍ በደጃፍ - አረንጓዴ አሻራችንን እናሳርፍ'' በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ በመዲናዋ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በሚገኘው ጌዲኦ ዋሻ ችግኝ ተክለዋል።

ወጣቶቹ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አገራዊ ጥሪ መሰረት በክረምት ወራት 2 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል የያዙትን ዕቅድ ዛሬ 500 ችግኞችን በመትከል ጀምረዋል።

የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ፕሬዚዳንት ወጣት አዕምሮ አዱኛ እንደገለጸው በተያዘው ክረምት በከተማ አስተዳደሩ 7 ነጥብ 2 ሚሊዮን ችግኝ የሚተከል ሲሆን ከዚሁ ውስጥ 2 ሚሊዮን ያህሉ  በወጣቶቹ ሊግ የሚሸፈን ይሆናል።

ችግኝ መትከል ብቻም ሳይሆን የመንከባከብና የማጽደቅ ተግባራት ዓመቱን ሙሉ የሚተገበሩ ይሆናል ብሏል።

የሊጉ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወጣት በቀለ ታጀበ በበኩሉ አገራዊውን አረንጓዴ አሻራ የማሳረፍ ጥሪ በመቀበል በተለይ ወጣቶች ሊተጉ እንደሚገባ አመልክቷል።

ዛሬ አረንጓዴ አሻራን ማሳረፍ ነገ የተሻለች አገር የሚረከበውን ትውልድ ለማገዝ የሚሰራ የቤት ስራ መሆኑን በመግለጽ ሁሉም የድረሻውን ሳይታክት እንዲወጣም አሳስቧል።

የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን ሽታ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ የቀረበበትን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለማሳካት 'ወጣቱ በትጋት እየሰራ ይገኛል' ብለዋል።

በመዲናዋ የሚገኙ ወጣት ባለሃብቶችን በማስተባበር ችግኝ እንዲተክሉና ዕለት በዕለትም የመንከባከብ ስራ በዘላቂነት እንዲሰሩ እያስተባበሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ጎን ለጎን የኮሮናን ቫይረስ ለመዋጋት ወጣቱን በማስተባበር የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎች እየተሰሩ ሲሆን ችግኝ ተከላ ሲካሄድም ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ እንደሚሆን አስታውሰዋል።

በዘንድሮው ክረምት በአገር አቀፍ ደረጃ የ5 ቢሊዮን ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ተጀምሮ ርብርብ እየተረገ መሆኑ ይታወቃል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም