የኢትዮጵያ አየር መንገድ ''ስኬት ስኬታችን፤ ጉድለቱ ጉድለታችን ነው''- ታዋቂ ሰዎች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ''ስኬት ስኬታችን፤ ጉድለቱ ጉድለታችን ነው''- ታዋቂ ሰዎች
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 04/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ''ስኬት ስኬታችን ነው፤ ጉድለቱ ጉድለታችን ነው'' ሲሉ ታዋቂ ሰዎች ዛሬ ተናገሩ። የኪነጥበብና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችን ያካተቱ ሰዎች አየር መንገዱን ጎብኝተዋል።
አየር መንገዱ ባዘጋጀው ጉብኝት ላይ የተሳተፉት ታዋቂ ሰዎች በሰጡት አስተያየት አየር መንገዱ ብሔራዊ ኩራት በመሆኑ በስኬቱም በጉድለቱም አብረው መሆናቸውን ገልጸዋል።
የጉብኝቱ አስተባባሪ አቶ ዮናስ ጂ. ዓለሙ አየር መንገዱ የአገር ሀብት በመሆኑ በውጤታማነቱም በችግሩም አብረው በመሆናቸውን በጉብኝቱ መሳተፋቸውን ገልጸዋል።
''አየር መንገዱ ተራ የንግድ ድርጅት አይደለም። እኛ ኢትዮጵያውያን በአየር መንገዳችን የምንቀየምበት ጉዳይ ካለ፤ የእናት ገመና ወደ ውጭ አይወጣምና በጋራ ተወያይተን ለተቀየምንበት ጉዳይ በጋራ መፍትሄ እንፈልጋለን'' ብለዋል።
''የአየር መንገዱ ሠራተኞች ክንፍ ያላቸው መላዕክት ናቸው ብዬ ለመከራከር አልደፍርም። ነገር ግን አየር መንገዱ መገለጫዬና ክብሬ በመሆኑ ሰድቦ ለሰዳቢ የሚሰጥ ዜጋ ሲያጋጥመኝ ግን የነካውን ኢትዮጵያዊነቴን ነውና ባለኝ አቅም ሁሉ ታግዬ እንዳስቆም የማንም ፈቃድ አያስፈልገኝም'' ሲሉም አቶ ዮናስ ተናግረዋል።
የአየር መንገዱን ሥራዎች በመመልከቱ ደስተኛ መሆኑንና ባየው እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ኩራት ተሰምቶኛል ሲል አርቲስትና የማስታወቂያ ባለሙያ ሠራዊት ፍቅሬ ተናግሯል።
አየር መንገዱ አገርንም አህጉሩንም የሚያኮራና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚያደርገው ተግባር እያከናወነ መሆኑን ተመልክተናል ያለው ሌላው ጋዜጠኛ በፍቃዱ አባይ ነው።
''አየር መንገዱ ውስጥ እየተደረጉ ያሉት ለውጦች በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያኮሩ ናቸው'' ያሉት ደግሞ ሌላው ታዋቂ ሰው ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡ ናቸው።
ሁሉም ተቋማት እንደ አየር መንገዱ ሥራቸውን በትጋት ሊስሩ ይገባል በማለትም ምክራቸውን ለግሰዋል ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካውያንም ኩራት ስለሆነ በጥንቃቄ ልንይዘው ይገባል በማለት አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ አሳስቧል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም የጉብኝቱን ተሳታፊዎች አመስግነው፤ጉብኝቱ በአየር መንገዱ ያለውን እውነታ ለማወቅ እንዳስቻላቸው እምነታቸውን ገልጸዋል።
አየር መንገዱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚያደርገውን ዘመናዊ መሠረተ ልማት ማስፋፊያ ሥራዎች እያከናወነ መሆኑ በዚህ ወቅት ተመልክቷል።