ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት አማካይ ዓመታዊ ዕድገቷ 10 ነጥብ 2 ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 04/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት አመታዊ የኢኮኖሚ ዕድገቷ 10 ነጥብ 2 ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅ የፌዴራል ፕላንና ልማት ኮሚሽን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ የአስር ዓመት የልማት መሪ ፕላን ረቂቅ ላይም በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ውይይት ተካሂዷል።

የፕላንና ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ፍጹም አሰፋ የአስር ዓመት የልማት እቅድ ረቂቁን ለክልል ፕሬዚዳንቶች፣ ለሚኒስትሮችና ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ገለጻ አድርገዋል።

በእቅዱ መሰረት ኢትዮጰያን አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት የማድረግ ራዕይ መያዙንም ዶክተር ፍጹም አብራርተዋል።

እቅዱ አገሪቷ በቀደሙት ዓመታት ስታወጣቸው ከነበሩ የልማት እቅዶች የተለየና የዜጎችን የኑሮ ደረጃ በተጨባጭ ሊያሻሽል የሚችል መሆኑንም ገልጸዋል።

እንደ ዶክተር ፍጹም ገለጻ ከእቅዱ መነሻዎች ውስጥ ያለፉት ዓመታት አፈጻጸም፣ ራዕይ 2022፣ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እንዲሁም አለም አቀፍና አህጉራዊ ስምምነቶች ይገኙበታል።

ኢትዮጵያ በተለይም በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜኝን እቅዷ የዘጠኝ በመቶ አማካይ ዓመታዊ ዕድገት ማስመዝገብ ብትችልም ይህን ማስቀጠል አልቻለችም ነው ያሉት።

በአለም አቀፉ የኮቪድ 19 ወረርሽኝና በሌሎችም ምክንያቶች የ2012 የአገሪቷ ዓመታዊ ዕድገትም 6 በመቶ እንደሚሆን ይጠበቃል።

በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ይተገበራል በተባለው መሪ እቅድ የአገሪቷ አመታዊ አማካይ የኢኮኖሚ ዕድገት 10 ነጥብ 2 በመቶ እንደሚሆን ነው ዶክተር ፍጹም የገለጹት።

ግብርና፣ አምራች ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝም፣ ከተማ ልማት፣ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ በእቅዱ ትኩረት የተሰጣቸው ዘርፎች ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም