የሕዝብና ቤት ቆጠራ ለሦስተኛ ጊዜ ተራዘመ - ኢዜአ አማርኛ
የሕዝብና ቤት ቆጠራ ለሦስተኛ ጊዜ ተራዘመ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4/2012 (ኢዜአ) የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባካሄዱት የጋራ ስብሰባ የሕዝብና ቤት ቆጠራ ለሦስተኛ ጊዜ እንዲራዘም ወሰኑ።
ሁለቱ ምክር ቤቶች በዛሬው ዕለት አምስተኛ ዓመት 1ኛ ልዩ የጋራ ስብሰባቸውን አካሂደዋል።
ምክር ቤቶቹ በኮቪድ- 19 ሳቢያ አራተኛውን የሕዝብና ቤት ቆጠራ ማካሄድ ስለማይቻል እንዲራዘም በቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ላይ ሰፊ ውይይት አድርገዋል።
በጉዳዩ ላይ የምክር ቤቱ አባላት ረዘም ያለ ጊዜ ፈጅተው ተከራክረውበታል።
በተለይም በዚህ ወቅት የሕዝብ ቆጠራ ማድረጉ ለሕዝብ ደህንነት አደጋ ከመሆኑም በላይ ለሀገር የሚጠቅም ትክክለኛ መረጃ ማግኘት እንደማይቻል ከአባላቱ ተነስቷል።
ከዚህ ሀሳብ በተቃራኒ ደግሞ አንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት ቆጠራው መካሄድ አለበት የሚል ሀሳብ አራምደዋል።
የምክር ቤቱ አባላት ሰፊ ክርክር ካደረጉ በኋላ ቆጠራው ቢካሄድ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት በመገንዘብ እንዲራዘም ወስነዋል።
በውሳኔው መሠረትም የኮቪድ- 19 ወረርሽኝ መፍትሔ ማግኘቱ በዓለምና በሀገር አቀፍ ደረጃ በተረጋገጠ በሁለት ዓመት ውስጥ ቆጠራው የሚከናወን ይሆናል።
ውሳኔው በ5 ተቃውሞ፣ በ13 ድምጸ ተአቅቦ የውሳኔ ሀሳብ ቁጥር 1/2012 ሆኖ በአብላጫ ድምፅ ጸድቋል።
በተያያዘ ዜና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 16ኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዶ የተለያዩ አዋጆችን መርምሮ አጽድቋል።
በዚህም የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክርቤትንና የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስልን ሕጋዊ ሰውነት ለመስጠት የቀረቡ ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ አጽድቋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ሕጋዊ ሰውነት የተሰጠበት ረቂቅ አዋጅም በአንድ ተቃውሞ በአብላጫ ድምፅ ጸድቋል።
የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ሕጋዊ ሰውነት ረቂቅ አዋጅ በሁለት ተቃውሞና በሁለት ድምፀ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ ጸድቋል።
የመንግሥት ልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ለማዘዋወር የቀረበ ረቂቅ አዋጅንም ምክር ቤቱ በ16 ተቃውሞ በሦስት ድምፀ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል።
ምክር ቤቱ በፌዴራል መንግሥት የ2013 ረቂቅ በጀት ላይ በመወያየትም ለበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።