ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለፉት 11 ወራት የ31 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ምርት አገበያየ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለፉት 11 ወራት የ31 ቢሊዮን ብር ምርት ማገበያየቱን አስታወቀ።

በግብይቱ 698 ሺህ 349 ቶን የተለያዩ ምርቶች ግብይት የተካሄደ ሲሆን ይህም ካለፈው ዓመት ተመሣሣይ ወቅትጋር ሲነጻጸር በተገበያየው የምርት መጠን 10 በመቶ፣ በገንዘብ ደግሞ 16 በመቶ ብልጫ ማሳየቱን ምርት ገበያ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ምርት ገበያው ካገበያያቸው ምርቶች ውስጥ 281 ሺህ ቶን ቡና በ22 ነጥብ 3 ቢሊዮን፣ 240 ሺህ ቶን ሰሊጥ በ10 ነጥብ 4 ቢሊዮን፣ 76 ሺህ ቶን አኩሪ አተር በ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን፣ 51 ሺህ 361 ቶን አረንጓዴ ማሾ በ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር መሸጣቸውን ጠቅሷል።

ከዚህ በተጨማሪ ነጭ ቦሎቄና ቀይ ቦሎቄ በግብይቱ ውስጥ የተካተቱ ሲሆን ከጠቅላላው ግብይት ቡና የ40 በመቶ እንዲሁም ሰሊጥ የ34 በመቶ ድርሻ በመያዝ ቀዳሚ ሆነዋል።

የዚህ ዓመት የቡና ግብይት ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በመጠን በ1 በመቶ፤ በዋጋ ደግሞ በ19 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በ11ዱ ወራት ውስጥ የዕቅዱን 96 በመቶ ማሳካቱን በመግለጫው ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም