ቀጥታ፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከሳዑዲ ዓረቢያ አምባሳደር ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 4/2012(ኢዜአ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በኢትዮጵያ የሳዑዲ ዓረቢያ አምባሳደር ሳሚ ጀሚል አብዱላሂን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ፡፡

ሳዑዲ አረቢያ በአገሯ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለምታደርገው ድጋፍም አመስግነዋል።

ውይይቱ በሳዑዲ ዓረቢያ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ በሁለቱ አገሮች ግንኙነትና  በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ያተኮረ ነበር።

አቶ ገዱ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ኢትዮጵያ ከሳዑዲ ዓረቢያ ጋር ያላትን  ረጅም ዘመናትን  ያስቆጠረ ታሪካዊ፣ ሁሉን አቀፍ ወንድማዊ ወዳጅነት  ወደ ላቀ  ደረጃ  ለማሸጋገር ትሰራለች ብለዋል።

ሳዑዲ ዓረቢያ በአገሯ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን  ለምታደርገው ድጋፍም አመስግነው፤ 

ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ወደ አገሯ በሚገቡ የውጭ ዜጎች ያለባትን  ጫና  እንገነዘባለንም  ብለዋል  ሚኒስትሩ፡፡

ኢትዮጵያም ከሳዑዲ ዓረቢያ ጋር ተቀራርባ መሥራቷን እንደምትቀጥልም ተናግረው፤  አገሮቹ ያላቸው  የዲፕሎማሲ  ተሞክሮ በአቅም  ግንባታና  በልምድ  ልውውጥ   እንዲጠናከር አቶ ገዱ ጠይቀዋል፡፡

በሦስቱ የተፋሰሱ አገሮች መካከል ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውይይት  ጋር  ያለውን  ጉዳይም አብራርተውላቸዋል።

አምባሳደር አብዱላሂ በበኩላቸው ሳዑዲ ዓረቢያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር እንደምታጠናክር ገልጸዋል።

ወደ አገራቸው ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የሚገቡ የውጭ ዜጎች የሚፈጥሩትን ጫና ኢትዮጵያ  በመገንዘቧ አመስግነዋል።

አገራቸው ሁለቱ አገሮች ካላቸው የካበተ የዲፕሎማሲ  ልምድ አንጻር በአቅም ግንባታ ላይ  እንዲያተኩሩ ትሰራለች ብለዋል።

ከግድቡ ጋር በተያያዘ ሦስቱ አገሮች ያላቸውን ልዩነት በውይይት እንዲፈቱ  እንደምትሻም አምባሳደሩ ገልጸዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም