የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 04/2012 (ኢዜአ) የኢፌድሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ጆሃን ቦርግስታምን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ።
የአውሮፓ ህብረት በኮሮናቫይረስ መከላከል የኢትዮጵያን ጥረት በመደገፍ ላደረገው አስተዋፆም አቶ ገዱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ህብረት ጋር ባላት ስትራቴጂካዊ እና ሁሉን አቀፍ ትብብር ደስተኛ መሆናቸውን አቶ ገዱ በውይይቱ ወቅት ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ይህንን ግንኙነት በተሻለ ሁኔታ አጠናክራ ለማስቀጠል በትኩረት ትሰራለችም ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የጤና ስጋት የሆነውን የኮሮና ወረርሽኝ ለመከላከል በምታደርገው ጥረት የአውሮፓ ህብረት እያደረገ ስላለው ድጋፍም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ ከዚህ ቀደም የጀመሩትን ውይይት ለማስቀጠል በሚያደርጉት ውይይት የአውሮፓ ህብረት በታዛቢነት በመሳተፉ ኢትዮጵያ ደስተኛ መሆኗንም አቶ ገዱ ገልጸዋል።
ግድቡ የደረሰበትን ደረጃና እስከ ዛሬ ድረስ በሶስቱ አገሮች የተደረጉ ውይይቶችን በተመለከተም ለአምባሳደሩ ገለጻ አድርገዋል።
በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ጆሃን ቦርግስታም በበኩላቸው የአውሮፓ ህብረት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል እያደረገች ያለውን ጥረት በማድነቅ የአውሮፓ ህብረት በዚህ በኩል የሚያደርገውን ድጋፍም አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ሶስቱ አገሮች ከግድቡ ጋር በተያያዘ ያላቸውን ልዩነት በውይይት እንዲፈቱ የአውሮፓ ህብረት ፋላጎት መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም የአውሮፓ ህብረት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ አምባሳደሩ መግለፃቸውን የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት አስታውቋል።