የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማት አመራሮች ደም ለገሱ - ኢዜአ አማርኛ
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማት አመራሮች ደም ለገሱ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 4/2012(ኢዜአ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማት አመራሮች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ያጋጠመውን የደም ዕጥረት ለመቅረፍ ደም ለገሱ።
ኮቪድ-19 በኢትዮጵያ መከሰቱን ተከትሎ የደም ዕጥረት እንዳጋጠመውና ህብረተሰቡ ደም እንዲለግስ የጤና ሚኒስቴር ጥሪ ማስተላለፉ ይታወቃል።
ለጥሪው ምላሽ ለመስጠት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከፍተኛ የሥራ አመራሮችና የተጠሪ ተቋማት አመራሮች በዛሬው ዕለት ደም ለግሰዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚንስትር ዴኤታ አቶ ሲሳይ ቶላ የተቋሙ ሠራተኞች በተለያዩ ጊዜያት የደም ልገሳ ተግባር ሲያከናውኑ መቆየታቸውን አስታውሰው፣ በዛሬው ዕለት ደም የለገሱትም በመንግስት ለተደረገው ጥሪ ምላሽ ለመስጠት ታስቦ መሆኑን አስረድተዋል።
በኮቪድ-19 ምክንያት በጽኑ ሕሙማን ክፍል የሚገኙ ታማሚዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ ደም እንደሚያስፈልጋቸውም ተናግረዋል።
በቀጣይ ፈቃደኛ የሆኑ የተቋሙ አመራሮች በብሔራዊ የደም ባንክ አገልግሎት በየሦስት ወሩ ደም ለመለገስ ምዝገባ ማካሄዳቸውንም ሚንስትር ዴኤታው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ጨረር መቆጣጠር ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር መብራቱ ገብረማርያም በበኩላቸው ተቋሙ በኮቪድ-19 መከሰት ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የምግብና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል።
አሁንም የወረርሽኙን መከሰት ተከትሎ የጤና ሚኒስቴር የደም እጥረት እንደገጠመ ላስተላለፈው መልዕክት ምላሽ ለመስጠት ሁሉም ሠራተኛ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ በቀጣይም ተቋሙ ከድህረ ኮቪድ በኋላ ያሉ ችግሮችን በጥናት ለይቶ ለመፍታት የድርሻውን ለማበርከት እንደሚሰራ ዶክተር መብራቱ ገልጸዋል።
በደም ልገሳ መርሃግብሩ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አመራሮች፤ በተቋሙ ስር ያሉት የኢትዮጵያ ባዮ-ቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት፣ የጅኦ ስፓሻል ኢኒስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ ጨረር መቆጣጠር ባለስልጣንና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት ተጠሪ ተቋማት አመራሮች ደም ለግሰዋል።