ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ እየተካሄደ ያለውን ውይይት በተመለከተ ያላትን አቋም አሳወቀች

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4/2012(ኢዜአ) ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ እያካሄዱት ባለው ድርድር ኢትዮጵያ ያላትን አቋም ግልጽ ማድረጓን የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚያድርጉት የሶስትዮሽ ድርድር እንደቀጠለ ነው።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ የሙሌትና አለቃቅ በሚመለከት በኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ መካከል የሚደረገው የሶስትዮሽ ድርድር በየአገራቱ በውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደረጃ እየተካሄደ ነው።

በበይነ-መረብ የቪዲዮ ኮንፈረንስ የሚካሄደው ውይይት ደቡብ አፍሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት እና አሜሪካን በታዛቢነት አስቀምጧል።


የታዛቢዎቹ ሚና ምን ይሁን በሚለው ጉዳይ በአገራቱ መካከል መግባባት ላይ ባይደረስም የግድቡ የመጀመሪያ ሙሌት እና ዓመታዊ የውሃ አለቃቅ ላይ ተወስኖ የሶስቱ ሀገራት ድርድር ቀጥሏል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ልዩነቶችን በድርድር ለመፍታት ኢትዮጵያ እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም ዝግጁ መሆኗን በውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሯ በኩል አስረድታለች።

በመድረኩ ላይ ኢትዮጵያ ለእውነተኛ ውይይትና ድርድር በውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደረጃ ለማስቀጠል ቁርጠኛ ስለመሆኗ፣ የ2015 የሕዳሴ ግድብ የጋራ መርህ ስምምነት በሙሉ እንዲከበርም አቋሟን ገልጻለች።

የታዛቢዎች ሚናም ድርድሩን በመታዘብና  በሶስት አገራት የጋራ ፍላጎት ሲጠሩ ልምዳቸውን ከማጋራት ውጭ ያለፈ ሚና ሊኖራቸው እንደማይገባ ታምናለች።

ድርድሩ በባለፈው የካቲት ወር በወጣው የቴክኒካል ቡድኑ የስራ ማንዋል መሰረት እንዲቀጥል ፍላጎቷ መሆኑን አስታውቃለች።

በመጀመሪያው ቀን ውይይትም ከማክሰኞ፣ አርብ፣ ዕሁድ በስተቀር ድርድሩ እስኪጠናቀቅ ድረስ እንዲቀጥል ስምምነት ተደርሷል።

በሶስቱ አገራት መካከል ያለው ስምምነት በመተማመንና በሃቀኛ መንገድ መመራት እንዳለበትም ኢትዮጵያ ታምናለች።

በድርድሩ ቀጣይነት አምና የገባችው ግብጽ በሌላ በኩል ለሁለተኛ ጊዜ ለጸጥታው ምክር ቤት ያስገባችው አቤቱታ በድርድሩ ላይ ላላት እምነትና ግልጸኝነት የሚያጠራጥር መሆኑንም ኢትዮጵያ ጠቅሳለች።

በመሆኑም ሁሉም ወገኖች በግድቡ የመጀመሪያ ዙር ውሃ አሞላልና አለቃቅ ጉዳይ ወደ ትክክለኛ ምክክርና ድርድር እንዲመጡ ጥሪ አቅርባለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም