ቀጥታ፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከዓለማችን ድንቅ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ መሆኑ ተጠቀሰ

ሰኔ 4/2012(ኢዜአ) በዚህ ዘመን በዓለም ላይ ድንቅ ከሚባሉት ግዙፍ ፕሮጀክቶች መካከል ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አንዱ መሆኑን ዘ ብሉቢም የተባለ የመረጃ ምንጭ ዘግቧል።
ዓለም በርካታ ግዙፍና አስደናቂ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በማከናወን ላይ መጠመዷን በ2020 በብሉቢም የተዘጋጀው አጭር ዘገባ ያመለክታል።

የዓለም አገሮች ፈታኝ ችግሮችን ተቋቁመው በተለያዩ የልማት መስኮች አዳዲስ፣ ግዙፍና አስደናቂ ሜጋ ፕሮጀክቶችን መገንባታቸውን ቀጥለዋል።

እንደገዘገባው ከሆነ አሜሪካ በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር የ2026ን የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ እንዲሁም የ2028ን ኦሎምፒክ ጌም ለማዘጋጀት ደፋ ቀና ማለት ጀምራለች።

አሁን ላይ ቅድሚያ በመስጠት እያከናወነች ያለችው ግዙፍና ዘመናዊ ኤርፖርት ግንባታም እንዲሁ።

አገሪቱ ወገቧን አጥብቃ የችካጎውን "ኦሂያዮ አውሮፕላን ማረፊያ" በ8 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ማስፋፋትና ማዘመን ጀምራለች።

በማስፋፊያ ስራው አውሮፕላን ማረፊያው 280 ስኩየር ሜትር ተጨማሪ ይዞታ የሚጎናጸፍ ሲሆን 50 ተጨማሪ የደንበኞች መስተናገጃ በሮችም (ጌትስ) ይኖሩታል ተብሏል።

እንደአውሮፓውያን አቆጣጠር በ2028 ለማጠናቀቅ ቀን የተቆረጠለትን የእዚህን ኤርፖርት የማስፋፊያ ግንባታ ሥራ ዘ ብሉቢም ከ2020 ግዙፍ ሜጋ ፕሮጀክቶች አንዱ ሲል አስቀምጦታል።

በ35 አገራት የጋራ ትብብር የግንባታው ሥራው በፈረንሳይ የተጀመረው ዓለም አቀፍ የኒውክሌር ምርምር ተቋም ፕሮጀክትም ሌላኛው ተጠቃሽ ግዙፍ የልማት ሥራ ተብሏል።

ሦስት ትላልቅ ሕንፃዎችን ያካተተውና በአሁኑ ወቅት የግንባታ ሥራው ከ60 በመቶ በላይ የደረሰው ይህ ፕሮጀክት የግንባታ ወጭው 20 ቢሊዮን ዶላር መሆኑ በሪፖርቱ ተገልጿል።

ሌላኛው የዘመናችን ተጠቃሽ ግዙፍ ፕሮጀክት የአፍሪካ የነፃነት አርአያና የሰው ልጅ መገኛ በሆነችው አገር እየተገነባ ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሆኗል።

ግድቡ በአፍሪካ እጅግ ድንቅ ከሚባሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች መካከል መሆኑ ተጠቅሷል። የግድቡ ግንባታ ይጠናቀቃል ተብሎ ቀደም ሲል ተቀምጦለት ከነበረው ቀነ ገደብ ቢዘገይም ለኢትዮጵያ ብሎም ለአካባቢው አገራት ቀጣይ ተስፋ ሲል ዘ ብሉቢም አስቀምጦታል።

ለግድቡ ግንባታ በአጠቃላይ 10 ሚሊዮን ቶን ኮንክሪት ይሞላል። የግድቡ ግንባታ ሲጠናቀቅም ከ6 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያመነጭና 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ የመያዝ አቅም እንደሚኖረው አስቀምጧል።

ለግድቡ ግንባታ ከ4 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጭ እንደሚጠይቅ በመጥቀስ ግንባታው ሲጠናቀቅም የኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚነት ትርጉም ባለው መልኩ የሚያሻሻል ይሆናል ብሏል ዘገባው።

በኢትዮጵያ ጥቅል ዓመታዊ ምርትም የስድስት በመቶ ድርሻ ሊኖረው እንደሚችልም ግምት አስቀምጧል።

የዓለማችን ፈጣኑ የጃፓን ዘመናዊ የባቡር ፕሮጀክት ግንባታም የዘመኑ ተጠቃሽ ዘመናዊ፣ ድንቅና ግዙፍ ፕሮጀክት ተብሏል፤ ፕሮጀክቱ በሁለቱ የጃፓን ከተሞች ቶኪዮና ናጎያ መካከል የ284 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ  አለው።

አዲሱና ፈጣኑ የባቡር ፕሮጀክት ግንባታ ሲጠናቀቅ ከአንደኛው ከተማ ወደ ሌላኛው ለመድረስ የሚወስደው ጊዜ 40 ደቂቃ ብቻ ይሆናል።

በሰዓት 500 ኪሎ ሜትር የሚምዘገዘገው ባቡር 90 በመቶ ጉዞው በምድር ውስጥ ለውስጥ እንደሚሆን ነው የተገለጸው።።

በአውስትራሊያ የሚገነባውና 271 ሜትር ርዝመት ያለው ባለ ስድስት ኮከብ ቅንጡ ሆቴልም ዘ ብሉቢም የሕዳሴውን ግድብ ጨምሮ ሌላው የዘመኑ ድንቅና ግዙፍ ፕሮጀክት ሲል ያስቀመጠው ነው።

ዘ ብሉቢም በዓለም ላይ ግዙፍ የኮንስትራክሽን ስራዎችን ተከታትሎ የሚያወጣ ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው የቪዲዮቻናል ሲሆን በየጊዜው የሚያወጣቸውን ዘገባዎችንም እስከ 11 ሚሊዮን የሚሆኑ የዓለም ሰዎች ይከታተሉታል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም