ቀጥታ፡

መገናኛ ብዙኃን የአገርን ጥቅም በሚያስጠብቁና የሕዝቡን የመረጃ ፍላጎት ማሟላት አለባቸው... ባለሙያዎች

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4/2012(ኢዜአ) መገናኛ ብዙኃን የአገርን ጥቅም በሚያስጠብቁና የሕዝቡን የመረጃ ፍላጎት በሚያሟሉ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ እንዲሰሩ የዘርፉ ባለሙያዎች ጠየቁ።

መገናኛ ብዙኃን የጋዜጠኝነትን ሥነ-ምግባር አክብረው በኃላፊነት እንዲሰሩም አሳስበዋል።

ባለሙያዎች ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ መገናኛ ብዙኃን ልዩነቶቻቸውንና ፍላጎታቸውን ወደ ጎን በመተው የአገርን ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ መረጃ ለሕዝቡ ለማድረስ በጋራ ሊሰሩ ይገባል።

የዋልታ ቴሌቪዥን የዜና ክፍል ዋና አዘጋጅ ጀማል ታመነ እንደገለጸው በአገሪቱ የሚከሰቱ ዓበይት ጉዳዮች የሚዘገቡበት ሁኔታ ወጥነት የጎደለውና የዘመቻ ሥራ በሚመስል መልኩ ነው።

ይህም ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይ ተከታታይነት ያለው ሥራ እንዳይሰራና የመረጃ ፍሰቱ እንዲቆራረጥ ያደርጋል ብሏል።

በተጨማሪም ዘርፉ ''ከምንም በላይ በኃላፊነት መስራትን ይጠይቃል'' ያለው ጋዜጠኛ ጀማል በአገራዊ ጥቅም ላይ መገናኛ ብዙሃኑ ያለድርድር በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክቷል።

በየጎረቤት አገሮች ተሞክሮን እንደ ልምድ በመውሰድ ለመልካም ነገር መጠቀም ተገቢ ነው ብሏል።

ይህም የሙያ ሥነ -ምግባሩን በጠበቀና የዜጎችን የመረጃ ፍላጎት በሚያሟላ መልኩ መሆን ይገባዋል አመልክቷል።

የአፍሪካን ሬኔሰንስ ቴሌቪዥን ሰርቪስ(አርትስ ቲቪ) የኦፕሬሽን ዋና ኃላፊ ጋዜጠኛ መላኩ ብርሃኑ በሰጠው አስተያየት በአሁኑ ወቅት መገናኛ ብዙኃን ሥነ ምግባርን በጠበቀና ባሟላ መልኩ እየሰሩ ነው ለማለት አያስደፍርም ይላል።

መገናኛ ብዙኃኑ በነጻነት የትኛውንም ዓይነት ዘገባ መስራት የሚችሉበት ጊዜ ቢሆንም፤ የአጠቃቀም ክፍተት እንደሚስተዋልም  ይናገራል።

በተለይም ለአንድ ወገን ያደላ ወይንም አንድን ወገን የሚተች በሚመስል መልኩ የሚሰራበት አግባብ እንዳለ መታዘቡን መላኩ አመልክቷል።

አገራዊ ጉዳዮች ላይ በስፋት ሽፋን ከመስጠት አኳያ ክፍተቶች እንደሚስተዋሉ ገልጾ፣ መገናኛ ብዙኃን ሕዝብን አንድ በሚያደርጉና ብሔራዊ መግባባትን በሚፈጥሩ ጉዳዮች ዙሪያ ተጽዕኖ መፍጠር ያለበትን ያክል ተደራሽ አይደለም ብሏል።

የሕዳሴ ግድብ ግንባታ፣የአረንጓዴ አሻራና ኮቪድ-19 ዋነኛ አገራዊ ጉዳዮች መሆናቸውን ጠቅሶ በነዚህና በሌሎች ተዛማች ጉዳዮች ላይ መገናኛ ብዙኃን ተከታታይነት ያለው ዘገባዎችን ሊሰሩ እንደሚገባው መላኩ አመልክቷል።

መገናኛ ብዙኃን የሕዝብን ጥቅም ለማስቀደም ግንባር ቀደም መሆን ይጠበቅባቸዋል ሲል አስተያየቱን የሰጠው ደግሞ የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን(ኢሳት)የአዲስ አበባ ስቱዲዮ ምክትል ዋና አዘጋጅና የኤዲቶሪያል አስተባባሪ ጋዜጠኛ ጌራ ጌታቸው ነው።

በተለይም ለሕዝቡ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ትክክለኛና ተዓማኒነት ያለው መረጃን ማድረስ እንደሚጠበቅም  ገልጿል።

ለዚህም ደግሞ ትኩረት የሚሹ አገራዊ አጀንዳዎች ላይ መገናኛ ብዙኃኑ ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን በመተው በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባም አስገንዝቧል።

በአገሪቱ በአሁኑ ወቅት በመገናኛ ብዙኃን በኩል በነጻነት የንግግር መብት በአንጻራዊነት እየተሰራበት መሆኑን የገለጸው ጌራ፤ይህንን ነጻነት በአግባቡ መጠቀም ተገቢ ነው ይላል።

በዋናነት መገናኛ ብዙኃን የሚያስተላልፉትን ዘገባ በኃላፊነት መስራት እንደሚጠበቅባቸው የሚደነግግና ተጠያቂ የሚያደርግ አሰራር በግልጽ አለመቀመጡ በዘርፉ የሥነ-ምግባር ጥሰት እንዲፈጸም ምክንያት መሆኑን አመልክቷል።

በመገናኛ ብዙኃን መካከል ያልተገባ ፉክክር  ዘንደ ይስተዋላል ያለው ጋዜጠኛ ጌራ፤ ይህም በሚተላለፈው መረጃ ላይ ወገንተኝነት እንዲጎላ ማድረጉን ገልጿል።

ለዚህም ደግሞ የሚመለከተው አካል የአሰራርና የመመሪያ ማሻሻያዎችን ማድረግ አለበት ብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም