ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ የሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌትና ዓመታዊ አለቃቀቅ ሰነዳቸውን አቀረቡ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ የሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌትና ዓመታዊ አለቃቀቅ ሰነዳቸውን አቀረቡ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌትና ዓመታዊ አለቃቀቅ ሰነዳቸውን አቅርበዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን የውሃ ሙሌትና ዓመታዊ የውሃ አለቃቀቅ በተመለከተ በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ መካከል ትናንት የተጀመረው በበይነ መረብ የታገዘ የሦስትዮሽ ድርድር ዛሬም ቀጥሎ ውሏል።
የሶስቱ አገራት ድርድር የዛሬ ውሎ የግድቡ የመጀመሪያ ሙሌትና ዓመታዊ አለቃቀቅ ላይ ብቻ የተወሰነ እንደሚሆን ተገልጾ ነበር።
በዚሁ መሰረት ሦስቱም አገራት የውሃ ሙሌትና ዓመታዊ አለቃቀቅ ሰነዳቸውን ማቅረባቸውን የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር በፌስቡክ ገጹ ያወጣው መረጃ ያመለክታል።
ውይይቶቹ የሚቀጥሉ ይሆናል ብሏል ሚኒስቴሩ።
አገራቱ ባቀረቧቸው የውሃ ሙሌትና ዓመታዊ አለቃቀቅ ሰነድ ላይ የተካተቱ ሀሳቦችና ቀጣይ የውይይት አጀንዳዎችን አስመልክቶ በሚኒስቴሩ መግለጫ ላይ የተባለ ነገር የለም።
ደቡብ አፍሪካ፣ አሜሪካና የአውሮፓ ኅብረት በሶስትዮሽ ድርድሩ ላይ በታዛቢነት እየተሳተፉ ነው።
በትናንቱ ድርድር አገራቱ የድርድር ስነ-ስርዓትን፣ ታዛቢዎችን፣ ስለ ድርድሩ አካሄድና ዋና ዋና የድርድር ያልተቋጩ ጉዳዮችን በተመለከተ ተነጋግረዋል።
አገራቱ እያንዳንዳቸው ዋና ዋና የድርድር ጉዳዮች ናቸው ያሏቸውን ሃሳቦች በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን ተከታታይ ውይይቶችን ለማካሄድ መግባባት ላይ መድረሳቸውም ተገልጿል።
ነገር ግን በትናንቱ የድርድር ጅማሮ የታዛቢዎቹ ሚና ምን ይሁን የሚለውን በተመለከተ በአገራቱ መካከል መግባባት ላይ አልተደረሰም ሲል ሚኒስቴሩ በመግለጫው አመልክቷል።