የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር የማሻሻያ አዋጅ ፀደቀ--የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

አዲስ  አበባ  ሰኔ 30/2010 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአዲስ አበባ አስተዳደር ቻርተር የማሻሸያ አዋጅን አፀደቀ። የማሻሸያ አዋጁ የስራ ዘመኑ ዛሬ ያጠናቀቀው  የከተሞቹ አስተዳዳር ምርጫ እስኪካሄድ እንዲመሩ የሚፈቅድና ምክትል ከንቲባ ከምክር ቤት አባል ውጭ እንዲሾም የሚፈቅድ ነው። ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 3ኛ አመት የስራ ዘመን 6ኛ ልዩ ስብሰባ ከህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቀረበለትን የሁለት ከተሞች ቻርተር ማሻሻያ አዋጅ መርምሮ አፅድቋል። ዛሬ የፀደቀው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 361/1995 የሚያሻሽል ነው። በከተማ  አስተዳደሩ በ2010 ዓ.ም  መካሄድ የነበረበት ምርጫ ባለመካሄዱ ምክንያት ምክር ቤቱንና አስፈፃሚ አካላትን እንደገና ማደራጀት ባለመቻሉ በቀጣይ ምርጫ ተከናውኖ እስከሚደራጅ አሁን ያለው የከተማው ምክር ቤትና ስራ አስፈፃሚ ስራውን ይዞ እንዲቀጥል ነው ማሻሻያው የተደረገው። በማሻሸያው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የምርጫ ጊዜ እንዲራዘም ከወሰነ ቀጣይ ምርጫ እስኪካሄድ የከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት ባለበት ይቀጥላል የሚል ንዑስ አንቀፅ ተካቷል። በአዋጁ አንድ ንዑስ አንቀፅ ተሰርዞ በምትኩ በምክትል ከንቲባነት ለመምራት ብቃት ያለው ሰው ለመምረጥ  ከምክር ቤት አባላት ወይም ክምክር ቤቱ አባላት ውጭ ለመሾም የሚቻልበትን ህግ የሚደነግግ ንዑስ አንቀፅ ተካቷል። የምክር ቤቱ የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጴጥሮስ ወልደሰንበት ከጠቅላይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት፣ከፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ፣ከከተማ አስተዳደሩ ሃላፊዎች ጋር ከተወያየ በኋላ ነው ለማፅደቅ ያመጣነው ብለዋል። ማሻሻያውም የስራ ዘመኑ ያበቃውን የምክር ቤቱ አስፈፃሚ አካለት ምርጫ እስኪካሄድ ህጋዊ የሚያደርግ መሆኑን ገልፀዋል። ከምክር ቤት አባል ውጭ ምክትል ከንቲባ እንዲመረጥ መካተቱም ብቃት ያለውን መሪ ለማግኘት እድሉን ያሰፋል ብለዋል። የስራ አስፈፃሚ አካላቱ የስራ ቆይታ ጊዜ ሲሻሻል የካቢኔዎቹስ የሚል ጥያቄ ከምክር ቤቱ አባላት ተነስቷል። አቶ ጴጥሮስ የካቢኔዎቹ የስራ ቆይታም ከአስፈፃሚው አካል ጋር የሚራዘም መሆኑን አብራርተዋል። የተሻሻለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ቻርተር አዋጅ በሁለት ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ አዋጅ ቁጥር 1094/2010 ሆኖ ፀድቋል። ተመሳሳይ ይዘት ያለውና አዋጅ ቁጥር 416/1996 የነበረው የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ በሶስት ተዓቅቦና በአብላጫ ድምፅ አዋጅ ቁጥር 1095/2010 ሆኖ ፀድቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም