በመጪዎቹ አስር ቀናት በኢትዮጵያና በደቡብ ሱዳን ከባድ ዝናብ ይጠበቃል - ኢጋድ - ኢዜአ አማርኛ
በመጪዎቹ አስር ቀናት በኢትዮጵያና በደቡብ ሱዳን ከባድ ዝናብ ይጠበቃል - ኢጋድ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3/2012 (ኢዜአ) በምዕራብ ኢትዮጵያና በአብዛኛው ደቡብ ሱዳን በቀጣዮቹ 10 ቀናት ከባድ ዝናብ ይጥላል ተብሎ እንደሚጠበቅ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን /ኢጋድ/ አስታወቀ።
ከመደበኛ ያለፈ ዝናብ በተወሰኑ የምስራቅ አፍሪካ አካባቢዎች ታይቶ የማይታወቅ ጎርፍ ሊያስከትል ይችላልም ብሏል።
ኢጋድ ከሰኔ 4 እስከ 13 ቀን 2012 ዓ.ም ባሉት 10 ቀናት በምስራቅ አፍሪካ ስለሚኖረው የአየር ሁኔታ ትንበያ አውጥቷል።
በተጠቀሱት ቀናት በአብዛኛው ደቡብ ሱዳን፣ በደቡባዊ ሱዳን አካባቢዎች፣ በምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በምዕራብና ሰሜን ምዕራብ ኬንያ በሚገኙ አካባቢዎች፣ በምዕራብና ሰሜን ዩጋንዳ አካባቢዎች እንዲሁም በደቡብ ምዕራብ ሶማሊያና በሶማሊያ የባህርዳርቻ ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ከ50 እስከ 200 ሚሊ ሜትር ዝናብ ሊጥል እንደሚችል ኢጋድ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።
በአስሩ ቀናት ውስጥ ከ30 ዲግሪ ሴልሺየስ በላይ የሆነ ከፍተኛ ዕለታዊ አማካይ የሙቀት መጠን በሱዳን፣ በኤርትራ፣ በጅቡቲ፣ በሰሜን ምስራቅ ኢትዮጵያና ሰሜን ሶማሊያ እንደሚጠበቅም ገልጿል።
ከ20 እስከ 30 ዲግሪ ሴልሺየስ አማካይ የሚባል ዕለታዊ የሙቀት መጠን በደቡብ ሱዳን፣ በአብዛኛው ዩጋንዳ፣ በሰሜን ምዕራብ ታንዛኒያና የታንዛንያ የባህርዳርቻ፣ ምስራቅና ሰሜን ምዕራብ ኬንያ፣ በአብዛኛው ሶማሊያ፣ ደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ድንበር አካባቢዎች ይኖራል ተብሎም ተገምቷል።
ከዚህ በፊት የነበሩ ትንበያዎች ኢትዮጵያን ጨምሮ በአንዳንድ የምስራቅ አፍሪካ አካባቢዎች ከመደበኛ መጠን ያለፈ ዝናብ ታይቶ የማይታወቅ የጎርፍ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል መጠቆማቸውም በመግለጫው ተወስቷል።
የብሔራዊ አደጋ ስራ አመራር ኮሚሽን በኢትዮጵያ በክረምቱ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ይጥላል ተብሎ በሚጠበቀው ዝናብ የሚከሰት ጎርፍ በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች እንዲፈናቀሉና ንብረቶች እንዲወድሙ ሊያደርግ እንደሚችል ማስጠንቀቁ ይታወሳል።
በግንቦት 2012 ዓ.ም በሶማሊያ፣ በኬንያና በሩዋንዳ በጣለው ከባድ ዝናብ ሳቢያ በተከሰተ ጎርፍ ከ300 በላይ ሰዎች ሕይወት ማለፉም አይዘነጋም።
ሶስቱ አገራት ጎርፉ በብርቱ የጎዳቸው ሲሆኑ ኬንያ በጎርፉ አደጋ ክፉኛ ተጎድታ ከ200 በላይ ዜጎቿም ሕይወታቸውን አጥተዋል።
በምዕራብ ዩጋንዳ የተከሰተው ጎርፍም በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎቿ ከቀዬአቸው እንዲፈናቀሉ አድርጓል።
ግንቦት 20 ቀን 2012 ዓ.ም በደቡብ ክልል ጋሞ ዞን በጋጮባባ ወረዳ ጋፀ እና ግና በሚባሉ ቀበሌዎች በተከሰተ የመሬት ናዳም የ10 ሰዎች ሕይወት ማለፉ የሚታወስ ነው።
አደጋው ከባድ ዝናብ ተከትሎ የተከሰተ ሲሆን በጋሞ ዞን መሰል አደጋዎች በተደጋጋሚ ይከሰታሉ።
በአጠቃላይ የተከሰተው ጎርፍ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ከቀዬአቸው ማፈናቀሉና ከሶስት ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ላይ የነበረ ሰብልም ማውደሙ ተገልጿል።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ የበረሃ አንበጣ መንጋና የጎርፍ አደጋ በአሁኑ ወቅት የምስራቅ አፍሪካ አገራትን እየፈተኑ ያሉ ክስተቶች ናቸው።
ሶስቱ ተደራራቢ ቀውሶች የምስራቅ አፍሪካን አገራት ወደ ከፋ የምግብ እጥረት ሊመሩ እንደሚችሉ የኢጋድ ዋና ጸሃፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በቅርቡ ገልጸው ነበር።
በኢትዮጵያም ግንቦት 22 ቀን 2012 ዓ.ም የተፋሰሶች ከፍተኛ ምክር ቤት በበይነ መረብ የተደገፈ 7ኛ መደበኛ ስብሰባውን ሲያካሂድ የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከፍተኛ የዝናብ ስርጭት በሚያስከትለው የጎርፍ አደጋ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እንዳይባባስ ተጋላጭ የሆኑ ተፋሰሶች የቅድመ መከላከል ስራቸው በፍጥነት እንዲጠናቀቅ አሳስበዋል።
ከክልሎች ጋር በመቀናጀት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን አሳሳቢነት ከግንዛቤ በማስገባት፤ ከፍተኛ የጎርፍ ስጋት የተደቀነባቸውን አካባቢዎች ቅድሚያ በመስጠት ወጪ ቆጣቢ በሆነ አግባብ የቅድመ መከላከል ስራዎች እንዲጠናቀቁ ምክር ቤቱ አቅጣጫ ማስቀመጡም አይዘነጋም።