ቀጥታ፡

የህዳሴ ግድብን ለማጠናቀቅ የልዩነት አስተሳሰብን በማስወገድ በአንድነት መንፈስ መስራት ይገባል

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3/2012 (ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ለማጠናቀቅ የልዩነት አስተሳሰብን በማስወገድ በአንድነት መንፈስ መስራት እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በመንግስት በኩል ግድቡን ለማጠናቀቅ የተወሰዱ እርምጃዎች የሚበረታቱ እንደሆኑም ነዋሪዎቹ ጠቅሰዋል።

የግድቡ አጠቃላይ አፈጻጸም ከ73 በመቶ በላይ ሲሆን በመጪው ክረምት ውኃ ለመያዝ የሚያስችሉ ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እንደተናገሩት፤ ከሁለት ዓመት በፊት የግድቡ ግንባታ ቀጣይነት ጥያቄ ውስጥ ገብቶ ነበር።

ከለውጡ በኋላ ግን ግድቡ ከገባበት ችግር በመላቀቅ እዚህ ደረጃ መድረሱ የሚያስመሰግነው መሆኑን ጠቁመው፤ ''ግድቡ አሁንም ቀሪ ስራዎች ያሉት በመሆኑ ሁላችንም በጋራ መስራት አለብን'' ነው ያሉት።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል አቶ ሲራክ መኮንን በግድቡ ዙሪያ የቃላት መወራወሮች ግድቡን እንዳይቀጥል ከማድረግ ውጭ የሚጠቅም ነገር እንደሌለው አመልክተዋል።

መንግስት ግድቡን ከፍጻሜ ለማድረስ እየተጋ መሆኑን ያነሱት አቶ ሲራክ፤ ''ተቀራርበን በመስራት ስኬት ማስመዝገብ አለብን'' ብለዋል።  

መንግሥት ብቻውን ውጤት ማምጣት ስለማይችል ህብረተሰቡ የሚችለውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅበት አመልክተዋል።

የተፈጠሩ ስህተቶች ታርመው ግድቡ ለዚህ መብቃቱ ደስ የሚያሰኝ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ አማረ ፈንቴ ናቸው።

ወይዘሮ መቅደስ ጉርሙ በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት መንግስት በዲፕሎማሲውም ሆነ በግድቡ ግንባታ ረገድ ጥሩ አያያዝ እንዳለው አንስተዋል።

''ከእኛ የሚጠበቀው እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፍ ማድረግ ነው'' ያሉት ወይዘሮ መቅደስ፤ የመንግስት ቁርጠኝነትና የህዝቡ አንድነት ግድቡን ከዳር ለማድረስ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።

ወጣት ይልማ ታነጋው የሌሎች አስተያየት ሰጪዎችን ሀሳብ እንደሚጋራ ገልጾ፤ እስካሁን ግድቡ የደረሰበት ደረጃ ትልቅ ቢሆንም ብዙ መስራት እንደሚያስፈልግ አብራርቷል።

የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክትን ለማጠናቀቅ የዲፕሎማሲ፣ የቴክኒክ፣ የውሃ ሙሌት፣ ገንዘብ የማሳባሰብና የተለያዩ ስራዎች በጥሩ ሁኔታ እየተካሄዱ እንደሚገኙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከትናንት በስቲያ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ መግለጻቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም