ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አበባ በአውሮፓ ገበያ መለያ ስሙን በዘላቂነት እያኖረ ነው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የአበባ ምርት በአውሮፓ ገበያ መለያ ስሙን /ብራንድ/ በዘላቂነት እያኖረ መሆኑን የኢትዮጵያ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አምራችና ላኪዎች ማኅበር ገለጸ።

የአበባ ምርት ከአገሪቷ የወጪ ንግድ ከአስር በመቶ በላይ የሚሆነውን ይሸፍናል።

የኮሮናቫይረስ መከሰትን ተከትሎም የኢትዮጵያ የአበባ ምርት በዓለም ገበያ ተፈላጊነቱ ጨምሯል።

የኢትዮጵያ አበባ መለያ /ብራንድ/ በአውሮፓና በመካከለኛው ምሥራቅ ስሙን ማስጠራትም ችሏል።

የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አምራችና ላኪዎች ማኅበር ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ዘውዴ ለኢዜአ እንደገለጹት ዘንድሮ የአበባ ገበያ ከፍተኛ መነቃቃት የታየበት ነው።

ምክንያቱ ደግሞ ኬንያ በጎርፍ መጥለቅለቋና የኮሮናቫይረስ መከሰትን ተከትሎ የአገሪቷ የካርጎ አገልግሎት ሰጪዎች ስራ በማቆማቸው የኢትዮጵያ አበባ በብቸኝነት ወደ ዓለም ገበያ መግባት በመቻሉ ነው ብለዋል።

የአበባ ምርት ውጤታማነት ይበልጥ እንዲጎለብት የመንግሥት ድጋፍ ቢኖርም፣ የእርሻ መሬት አቅርቦት ችግር አሁንም የዘርፉ ማነቆ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

ያም ሆኖ በዓለም ገበያ በርካታ የዘርፉ ባለሃብቶች የኢትዮጵያን አበባ የመግዛት ፍላጎት እንዳላቸው ነው የገለጹት።

አንድ ሺህ 700 ሄክታር በሚሆን መሬት የሚመረተው አበባ የማስፋፋት ሥራ እንደሚያስፈልገውም አንስተዋል።

የመሬት አቅርቦት ችግሩ ከተፈታና አገሪቷ የውሃ ሃብቷን መጠቀም ከቻለች በዘርፉ ተፎካካሪ ሆና መቀጠል እንደምትችልም አረጋግጠዋል።

የአበባ ወጪ ንግድ የማክሮ ኢኮኖሚውን ከመደገፍ አልፎ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ያወሱት አቶ ቴዎድሮስ፤ ለዘርፉ የሚሰጠው ትኩረት ከተጠናከረ የተሻለ ውጤት ማምጣት ይቻላል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአበባ አምራችነቷ በአፍሪካ ሁለተኛ በዓለም ደግሞ አራተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

የአበባ ምርቷ ወደ አውሮፓና መካከለኛው ምስራቅ አገራትና ሌሎችም የዓለም ገበያዎች እየገባ ሲሆን  ሰሜን አሜሪካ፣ ሩቅ ምስራቅና ቻይና ላይም የማስተዋወቅ ሥራ እየተሰራ ነው ተብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሰሞኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ለምክር ቤቱ አባላት በሰጡት ማብራሪያ ባለፉት 10 ወራት ከአበባ ወጪ ንግድ 440 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም