በትግራይ ለኮሮና መከላከል የሚረዳ 679 ሺህ ብር ድጋፍ ተገኘ - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ለኮሮና መከላከል የሚረዳ 679 ሺህ ብር ድጋፍ ተገኘ
መቀሌ፣ ሰኔ 03/2012 ( ኢዜአ) በትግራይ ክልል የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የሚረዳ 679 ሺህ ብር በጥሬ ገንዘብና ዓይነት ድጋፍ ተገኘ።
ድጋፉ የተገኘው በመቀሌ ከተማ ከሚገኙ ሁለት ማህበራት እና አንድ የእግር ኳስ ክለብ ነው።
የክልሉ ኮሮና መከላከል የገቢ ማሰባሰብ ንኡስ ግብረ ኃይል አስተባባሪ አቶ ዳንኤል አሰፋ ዛሬ የተረከቡት ድጋፍ ቫይረሱን ለመከላከል በሚደረገው እንቅስቃሴ ያለውን የገንዘብ እጥረት ለማቃለል እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
በዚህም የሸዊት አዮዲን ጨው አቅራቢዎች ማህበር 150ሺህ ብር በጥሬ ገንዘብ እና 50ሺህ ብር የሚያወጣ የስንዴ ዱቄት ለግብረ ኃይሉ አስረክቧል።
የማህበሩ ተወካይ አቶ ገብረመድህን ወልደስላሴ ያደረጉት ድጋፍ ትርፍ አግኝተው ሳይሆን ለወገናቸው አጋርነታቸውን ለማሳየት መሆኑን ገልጸዋል።
በመቀሌ ከተማ የፋሽን አልባሳት ክላስተር ማህበር 260 ሺህ ብር እና የደደቢት እግር ኳስ ክለብ ደግሞ 219ሺህ ብር ዛሬ ድጋፍ አድርገዋል።