"እንደማመጥ" የመገናኛ ብዙሃንና ጋዜጠኞች የቅስቀሳ መርሃ ግብር ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
"እንደማመጥ" የመገናኛ ብዙሃንና ጋዜጠኞች የቅስቀሳ መርሃ ግብር ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3/2012 (ኢዜአ) "እንደማመጥ" በሚል መሪ ሀሳብ ስለ ኮሮናቫይረስ ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ መፍጠርን ዓላማ ያደረገ የመገናኛ ብዙሃንና የጋዜጠኞች የቅስቀሳ መርሃ ግብር ዛሬ ተጀምሯል።
መርሃ ግብሩ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የስራ ኃላፊዎችና ጋዜጠኞች በአዲስ አበባ፣ በባህርዳር፣ በአዳማና ሐዋሳ ከተሞች ቫይረሱን አስመልክቶ ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ የሚፈጥሩበት መድረክ ነው።
በዚሁ መሰረት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ በመዲናዋ አራዳ ክፍለ ከተማ እንቅስቃሴ በሚበዛባቸው አካባቢዎችና የትራንስፖርት ስፍራዎች ቅስቀሳ አድርገዋል።
ዋና ስራ አስፈጻሚው የኮሮናቫይረስ ስርጭትን መከላከል የሚያስችሉ የጥንቃቄ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል።
ኅብረተሰቡ ቫይረሱን ለመከላከል ለሚያደርገው ጥንቃቄ መዘናጋት እያሳየ መሆኑንና ይህም ስርጭቱን ሊያሰፋው ስለሚችል ተገቢው ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስበዋል።
በአዲስ አበባ የቫይረሱ ስርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመሆኑ ስርጭቱን ለመግታት ነዋሪዎቿ የሚተላለፉ መልዕክቶችን በአግባቡ መተግበር አለባቸው ብለዋል።
በኮሮናቫይረስ የተያዙና በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ ያላቸው የሕክምና ባለሙያዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የገለጹት አቶ ሰይፈ ወረርሽኙ ከተስፋፋ ታማሚዎችን የሚያክም ባለሙያም እንደሚያንስ ጠቁመዋል።
የኅብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ የሕክምና ባለሙያዎችን በከፍተኛ ሁኔታ ማገዝ እንደሆነም አክለዋል።
ይህን የችግር ጊዜ ለማለፍ ከጤና ባለሙያዎች የሚተላለፉ መልዕክቶች እንዲተገበሩም ከአደራ ጭምር አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሕዝብ ግንኙነትና ስትራቴጂካዊ አጋርነት ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ ወንድይራድ በበኩላቸው ቅስቀሳውን ማድረግ ያስፈለገበትን ምክንያት አስረድተዋል።
ማኅበረሰቡ በመገናኛ ብዙሃን በየዕለቱ የሚተላለፉ መልዕክቶችን በመተግበር ቫይረሱ እንዳይዘመት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።
የአንቀጸ ምሕረት ቅዱስ ሩፋኤል ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ መልዕከ ምሕረት መምህር ቃለጽድቅ ከፍያለውም ራስን ከቫይረሱ መጠበቅ ኅብረተሰብን መጠበቅ በመሆኑ ሁሉም ጥንቃቄ ያድርግ ብለዋል።
እንደማመጥ" የመገናኛ ብዙሃንና የጋዜጠኞች የቅስቀሳ መርሃ ግብር ዛሬ ሲጀመር የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ የዋልታ ቴሌቪዥን፣ የአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ፣ የአማራ መገናኛ ብዙሃን ድርጅት፣ የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክና የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በተለያዩ ስፍራዎች ቅስቀሳ አድርገዋል።
የቅስቀሳ መርሃ ግብሩ እስከ ሰኔ 6 ቀን 2012 ዓ.ም ይቀጥላል።