የአዲስ አበባ ሞዴል ኢንተርፕራይዞችንና የቴክኖሎጂ ፈጠራ አሰልጣኞችን ተሸለሙ

79
አዲስ አበባ ሰኔ 30/2010 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ቢሮ 600 ሞዴል ኢንተርፕራይዞችንና የቴክኖሎጂ ፈጠራ አሰልጣኞችን ሸለመ። ሞዴል በሚል ተመርጠው ሽልማትና እውቅና የተሰጣቸው ኢንተርፕራይዞች በኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት በመታገዝ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የስራ ፈጣሪነት አቅማቸውን ማሳደግ የቻሉት ናቸው ። በከተማ አስተዳደሩ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘርኡ ሱሙር በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ በተዘጋጀው የሽልማትና እውቅና ስነስርዓት ላይ እንደተናገሩት ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን ተወዳዳሪ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው። የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ድጋፍ ከሚደረግላቸው ከ9ሺ በላይ ኢንተርፕራይዞች መካከል 478 ኢንተርፕራይዞች በካይዘን ትግበራ፣ በጥራትና ምርታማነት መሻሻል፣ በክህሎት፣ በቴክኖሎጂ እና በስራ ፈጠራ እውቅናና ሽልማት ተደርጎላቸዋል። የአዲስ አበባ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ በበኩላቸው በሀገሪቱ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ሰፊ ክፍተት በመኖሩ ሌሎች ኢንተርፕራይዞችም በሞዴልነት ከተመረጡት ተሞክሮ እንዲወስዱ ይደረጋል ብለዋል። የተሻሉ ሆነው ለተገኙ ኢንተርፕራይዞች ትልቁን ድርሻ የሚወስዱት አሰልጣኞች በመሆናቸው ጥረታቸውን እንዲቀጥሉ ከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ እንደሚያደርግም ተናግረዋል። በ2010 ዓ.ም የላቀ ቴክኖሎጂ ፈጠራና ሽግግር አሸናፊ የሆኑ 19 አሰልጣኞችና በተቋምና በቡድን ተወዳድረው አሸናፊ የሆኑ 89 አሰልጣኞች  የሜዳሊያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። በልዩ ሽልማት ዘርፍ ደግሞ ከአገልግሎት ውጪ የሆኑ 10 የአዲስ አበባ ከተማ አውቶብሶችን አገልግሎት እንዲሰጡ ያደረጉ የእንጦጦ የጀነራል ዊንጌት የንፋስ ስልክ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጂ በድምሩ 24 አሰልጣኞችም እውቅናና ሽልማት አግኝተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም