ቀጥታ፡

በሰብሎች ላይ የሚከሰቱትን ነቀዝና ተባዮችን ለመከላከል ፓኬጅ ተዘጋጀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2/2012 (ኢዜአ) በሰብሎች ላይ የሚከሰቱትን ነቀዝና ተባዮችን መከላከያ ፓኬጅ ከክልል ግብርና ቢሮዎች ጋር በቅንጅት መዘጋጀቱን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በዋናነት በግብርና፣ በሰብል ልማትና በእንስሳት እርባታ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ይታወቃል።

ዘርፉ ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ልማት የጀርባ አጥንት እንደሆነ የሚታመን ከመሆኑም ባሻገር 80 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚተዳደርበት እንደሆነም መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በኢትዮጵያ ባለፉት 10 ዓመታት የተገኘው ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት የምርትና ምርታማነት ማደግ ውጤት እንደሆነም ይነገራል።

በዚህም በተለይ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ለዘርፉ ዕድገት በዋናነት ትኩረት እንደሚሻ ይታወቃል።

ለዚህም በተለይ የሰብል ምርት በሚደርስበት ወቅት የአጨዳና የውቂያ ሥራዎችን በአግባቡ ማካሄድ እንደሚገባ የግብርና ሚኒስቴር ይገልጻል።

በሚኒስቴሩ የሰብል ልማት ዳይሬክተር አቶ ኢሣያስ ለማ ለኢዜአ እንደገለጹት በግብርናው ላይ በተለይ በድኅረ ምርት ጊዜ እስከ 30 በመቶ የሚከሰተውን የምርት ብክነት ለመቀነስ አርሶ አደሩ በወቅቱ ማጨድ ይገባዋል።

የነቀዝና ሌሎችም ተባዮችን በመከላከልም ምርቱ ጥራቱን በጠበቀ ደረጃ ወደ ገበያ ማቅረብም ጥቅም እንዳለው ይገልጻሉ።

ለዚህም ሚኒስቴሩ ከክልል ግብርና ቢሮዎች ጋር በመቀናጀት በሰብሎች ላይ የሚከሰቱትን ነቀዝና ተባዮችን የሚከላከሉበት ፓኬጅ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

ከማሣና በማዳበሪያ ዝግጅት ጀምሮ ተባይና ሌሎች በሽታዎችን በመከላከል ሂደት እንዲሁም አርሶ አደሩ የሚገጥሙትን ችግሮች ለመፍታትና ድጋፍ ለማድረግ እንደሚያስችል አስረድተዋል።  

በማዳበሪያ ሥርጭት በኩልም በአሁኑ ወቅት 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ለማሰራጨት ወደ ጅቡቲ እየገባ ሲሆን፤ እስካሁንም 73 በመቶ የሚሆነው ወደ አገር ውስጥ መግባቱን አስታውቀዋል።

እስካሁንም 41 በመቶ የሚሆነው ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም