ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም በሦስት ወር ውስጥ ብቻ ከ200 ሺህ በላይ ጎብኚዎችን አጥቷል

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም በሦስት ወር ውስጥ ብቻ ከ200 ሺህ በላይ የውጭ አገር ጎብኚ ቱሪስቶችን ማጣቱን ገለጸ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም በ1944 ዓ.ም የተመሠረተ ሲሆን በውስጡም አገሪቱን የሚያስተዋውቁ ቅሪቶችና ቅርሶች ይገኙበታል።

ሙዚየሙን በየጊዜው ወደ አገር ውስጥ የሚመጡ በርካታ የውጭ አገር ቱሪስቶችን ጨምሮ የአገር ውስጥ ጎብኚዎች በከፍተኛ ደረጃ እንደሚጎበኙት ይታወቃል።

ይሁንና በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ጫና ያሳደረው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከዚህ ቀደም የነበረውን የቱሪስት ፍሰት ማስቀረቱን የሙዚየሙ ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም አማረ ለኢዜአ ተናግረዋል።

ሙዚየሙ ወረርሽኙ በኢትዮጵያ ውስጥ ከተከሰተ በኋላ ከተዘጉና አገልግሎት ካቆሙ ተቋማት መካከል አንዱ ነው።


"ወቅቱ ከፍተኛ የጎብኚዎች ቁጥር ይስተናጋድበት የነበረ ከመሆኑ አንጻር ሲታይ ወረርሽኙ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሯል" ብለዋል።

ከመጋቢት እስከ ሰኔ ወር መጨረሻ ባለው ጊዜ ውስጥ እስከ 200 ሺህ የሚደርሱ የውጭ አገር ቱሪስቶች ሙዚየሙን እንደሚጎበኙት ይጠበቅ ነበር።

ይሁንና በዚህ ወቅት ወረርሽኙ መከሰቱ እነዚህን ቱሪስቶች እንዲያጣ ማድረጉን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም የሉሲ አጽምና ቀደምት የሰው ልጆች የሚጠቀሙባቸው የድንጋይ መሣሪያዎች ይገኙበታል።

በተጨማሪም ታሪካዊና አርኪኦሎጂካዊ ግኝቶች እንዲሁም በተለያዩ ኢትዮጵያዊያን የተሳሉና የተቀረጹ የሥዕልና የቅርጻ ቅርጽ ሥራዎች ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም