ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በሕዳሴ ግድብ ግንባታ ዙሪያ ከተፋሰሱ አገራት ጋር በሥምምነት ለመሥራት ብዙ ጥራለች--- ምሁራን

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን አስመልክቶ ከተፋሰሱ አገራት ጋር በትብብርና በሥምምነት ለመሥራት ከበቂ በላይ መጓዟን ምሁራን ገለጹ።

የዓባይ ውኃን በተመለከተ በተናጠል ሳይሆን ሁሉም የተፋሰሱ አገራት የተካተቱበት ድርድር ማድረግ እንደሚገባቸውም ምሁራኑ ገልጸዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ፣ ለግብፅና ለሱዳን ብቻ ሳይሆን ለአህጉሪቱም ከፍተኛ የትብብር ምንጭ እንደሚሆንም ገልጸዋል።

የዘርፉ ተመራማሪ የሆኑት ወይዘሪት መቅደላዊት መሳይ ለኢዜአ እንደገለጹት ሌሎች የተፋሰሱ አገራት ከዚህ በፊት ተመሣሣይ የመሠረተ ልማት ግንባታ ሲያካሂዱ ጥያቄ ያቀረበ አንድም አገር የለም።

አሁን ኢትዮጵያ እየገነባችው ባለው የሕዳሴ ግድብ ላይ ግን ተገቢነት የሌላቸው የተለያዩ ጥያቄዎች በተለይ በግብፅ በኩል ሲነሳ መቆየቱን ጠቅሰዋል።

ግብፅ ቀደም ሲል በግንባታው ላይ ጥያቄዎችን ስታነሳ የቆየች መሆኑን አስታውሰው አሁን ላይ ደግሞ የውኃ አሞላሉ ላይ ተገቢነት የሌላቸውን ጥያቄዎች ማስከተሏን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ግድቡን አስመልክታ ከአገራቱ ጋር በትብብርና በሥምምነት ለመሥራት ረጅም ርቀት መጓዟንም ተማራማሪዋ አብራርተዋል።

ግብፅና ሱዳን ያለ ማንም ጠያቂ ለበርካታ ዓመታት የዓባይን ወንዝ ሲጠቀሙበት የቆዩ መሆኑንም አስረድተዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ ዜጎቿን ከጨለማ ለማውጣት እየገነባችው ያለውን ግድብ ይጎዳናል የሚለው ሀሳብ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ተጠባባቂ ዲን ዶክተር ሣሙኤል ተፈራ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የታላቁ ሕዳሴ ግድብን በመለከተ በርካታ ዶክሜንቶችን ለሚመለከተው አካል ስታቀርብ ቆይታለች ብለዋል።

በመሆኑም በኢትዮጵያ በኩል እስካሁን በትብብርና በሥምምነት የግድቡን ግንባታ ለማስኬድ ሰፊ ርቀት መጓዟን ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ በዓለም ላይ ማንም ሀገር የራሱን ፕሮጀክት ለሌሎች አገራት ይፋ የማድረግም ሆነ የማማከር ሥራ የተለመደ አለመሆኑንም ዶክተር ሣሙኤል አስረድተዋል።

የዓባይ ውኃ ድርሻን በተመለከተ ሁሉም የተፋፈሱን አገራት ፍላጎት ባካተተ መልኩ ሊኬድበት የሚገባ መሆኑንም አንስተዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በመጪው ክረምት የመጀመሪያ ዙር 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ሚትር ኪዩብ ውኃ ለመሙላት ዝግጅት ተደርጓል።

የግድቡ አጠቃላይ አሁናዊ አፈጻጸምም 73 ነጥብ 7 በመቶ መድረሱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም