ቀጥታ፡

በወረኢሉ ወረዳ ለሁለት ሺህ አቅመ ደካሞች ድጋፍ ተደረገ

ደሴ፣ ሰኔ 2/2012 (ኢዜአ)  በደቡብ ወሎ ዞን የወረኢሉ ወረዳ አስተዳደር በኮሮና ቫይረስ ሥርጭት ምክንያት ለተቸገሩ ሁለት ሺህ አቅመ ደካሞች የምግብ እህል ድጋፍ ማደረጉን ገለጸ።

የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ሰለሞን ተፈራ እንደገለጹት የኮሮና ቫይረስ የሚያደርሰውን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጫና ለመቋቋም ሁሉም ሰው ሊረዳዳና ሊደጋገፍ ይገባል።

የወረዳው አስተዳደር በአገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆችን በማስተባበር አንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማሰባሰብ መቻሉን አውስተዋል።

በተሰባሰበው ገንዘብም ለሁለት ሺህ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙና አቅመ ደካማ የማኅበረሰብ ክፍሎች ዛሬ ድጋፍ ተደርጓል።

ድጋፉ 200 ኩንታል ዱቄት፣ 300 ኩንታል ሩዝና አራት ሺህ ሊትር ዘይት ያካተተ ሲሆን በነፍስ ወከፍ 25 ኪሎ ግራም እህልና ሁለት ሊትር ዘይት ተሰራጭቷል።

ድጋፍ የተደረገላቸው በቀን ሥራ ይተዳደሩ ለነበሩ፣ አረጋዉያን፣ አካል ጉዳተኞችና ሌሎች የዕለት ምግብ ለቸገራቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች መሆኑንም ገልጸዋል።

በቫይረሱ ምክንያት የሚደርሰውን ችግር ለማቃለል እየተሰራ ነው ያሉት አስተዳዳሪው የወረዳው ተወላጆች የአካባቢያቸውን ማኅበረሰብ አስበው ላደረጉት ድጋፍም ምሥጋና አቅርበዋል።

ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል ወይዘሮ ትሳሷ መዝገበ በሰጡት አስተያየት በኮሮና ቫይረስ መከሰት ምክንያት እየተዘዋወሩ የሚሰሩትን የቀን ሥራ በመቆሙ ለችግር መጋለጣቸውን አስታውሰዋል።

ዛሬ የተደረገላቸው ድጋፍ ችግራቸውን እንደሚያቃልልላቸው ገልጸው ድጋፍ ላደረጉትና ላስተባበሩት ሁሉ ምሥጋና አቅርበዋል።

ወይዘሮ አንሻ ይመር የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው በጣም በተቸገርኩበት ወቅት ድጋፍ በማግኘቴ በጣም ተደስቻለሁ ብለዋል።

ወረርሽኙን ለመቆጣጠር በቤታችን በመዋላችን ሰርተን መኖር አልቻልንም ያሉት ወይዘሮ አንሻ በሽታው እስኪጠፋ ድረስ በዘላቂነት የምንረዳበት መንገድ ሊመቻችልን ይገባል ብለዋል።

በደቡብ ወሎ ዞን እስከ አሁን በቫይረሱ ምንክንያት ለተቸገሩ ከ10 ሺህ ለሚበልጡ አቅመ ደካሞች ድጋፍ መደረጉንም ከዞኑ ኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም