ቀጥታ፡

የኮሮና ቫይረስን በመጠንቀቅ እንጂ በማግለል ልንከላከለው አንችልም- አሽከርካሪዎች

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 02/2012 (ኢዜአ) የድንበር ተሻጋሪ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ቫይረሱን ለመከላከል የቁሳቁስ እጥረት እንደገጠማቸውና በማህበረሰቡ መገለል እየደረሰባቸው መሆኑን ገለጹ።

የትራንስፖርት ሚኒስትሯ የአሽከርካሪዎቹ ችግር እንዲቃለል ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት( ኢዜአ) ያነጋገራቸው ከአዲስ አበባ ጂቡቲ ወደብ ተመላላሽ አሽከርካሪዎችን በየቦታው መገለል እየደረሰባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ አገር ውስጥ ከገቡ በኋላ ከተሞች ማግኘት ያለባቸውን እንደ ምግብ፣ውሃና ሌሎች አገልግሎት ማግኘት እንዳልቻሉም ጠቅሰዋል።

ተሽከርካሪዎቹ የሚያገለግሉት ኅብረተሰቡንና የሚጭኑትም ለማህበረሰቡ ፍጆታ የሚሆን አቅርቦት እስከሆነ ድረስ ሙያቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል።

ቫይረሱ የሚጠፋው ሁሉም ሰው ራሱን እየጠበቀ ሲተባበርና ሲደጋገፍ መሆኑን የጠቀሱት አሽከርካሪዎቹ፤ ማህበረሰቡ ከድርጊቱ እንዲቆጠብ አሳስበዋል። 

በሾፌሮች በኩል እንደ አገር የሚመከሩ ጥንቃቄዎችን እያደረጉ ቢሆንም፤ራሳቸውን ከቫይረሱ የሚከላከሉበት ቁሳቁስ እጥረት እንደገጠማቸው ተናግረዋል።

ለዚህም ማህበራት፣ባለንብረቶችና መንግሥት ትኩረት እንዲሰጧቸው ጠይቀዋል።

የትራንስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በበኩላቸው የድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች ከጤና ባለሙያዎች ቀጥሎ ለኢትዮጵያውያን መስዋዕትነት እየከፈሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በመሆኑም ማህበረሰቡ ይህን በማሰብ ራሱን ከቫይረሱ እየጠበቀ፣ በትብብር መንፈስ መሥራት እንጂ፤አሽከርካሪዎቹን ማግለል ተገቢ አይደለም ብለዋል።

ቫይረሱ ለመከላከል ከማህበራት ጋር ምክክር ከተደረገ በኋላ ጭምብል፣ሳኒታይዘርና መሰል ቁሳቁስ  ለአሽከርካሪዎቹ እንደሚታደላቸው ገልጸዋል።

በዚህ ረገድም በተለይ ባለንብረቶች ለአሽከርካሪዎቻቸው ቁሳቁሱን እንዲያቀርቡላቸው አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም