ቀጥታ፡

በሰሜን ወሎ ዞን የራያና ቆቦ ወረዳ አመራሮችን በመግደል የተጠረጠሩ ተያዙ

ወልዲያ፣ ሰኔ 2/2012 (ኢዜአ) በሰሜን ወሎ ዞን የራያ ቆቦ ወረዳ አመራሮችን በመግደል የተጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የዞን የሕዝብ ሰላምና ደህንነት መምሪያ ገለጸ።

የመምሪያው ኃላፊ ኮሎኔል ኃይለማርያም አምባየ ለኢዜአ እንደገለጹት ግለሰቦቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት የራያ ቆቦ ወረዳ አስተዳዳሪና የሰላምና ደህንነት ጽሕፈት ቤት ኃላፊን በመግደል ተጠርጥረው ነው።

ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ግድያው ከተፈጸመበት ግንቦት 23 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ፖሊስ፣ የልዩ ኃይል አባላትና ሌሎች የፀጥታ አካላት በቅንጅት በተካሄደው ጠንካራ የክትትል ሥራ ሊያዙ መቻላቸውን ተናግረዋል።

ግለሰቦቹ በቁጥጥር ሥር በዋሉበት ወቅትም አንድ ሽጉጥና አንድ ክላሽንኮቭ መሣሪያ ይዘው መገኘታቸውን ገልጸዋል።

በአመራሮቹ ግድያ የተጠረጠሩት ግለሰቦች ሰኔ 1 ቀን 2012 ዓ.ም በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ በሰጡት የእምነት ክህደት ቃል ድርጊቱን መፈጸማቸውን አምነው ለግድያ የተጠቀሙበትን መሣሪያ ጭምር ማስረከባቸውን ተናግረዋል።

ግለሰቦቹ ወንጀሉን ብቻቸውን እንደፈጸሙት በማመናቸውና ከመያዛቸው በፊት እነሱ ብቻ እንደፈጸሙት ይታመን እንደነበር የገለጹት ኃላፊው አሁን ላይ ፖሊስ ክትትሉን አቁሞ ተጠርጣሪዎቹን የመመርመር ሥራ መጀመሩን አብራርተዋል።

የወንጀሉን ምርመራ በፍጥነት በማካሄድም ለዐቃቤ ሕግ ቀርቦ በቅርቡ ክስ እንደሚመሰረትባቸው ኮሎኔል ኃይለማርያም አስታውቀዋል።

ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል በተደረገው እንቅስቃሴ የአገር ሽማግሌዎችና የአካባቢው ማኅበረሰብ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በመተባበር ላደረጉት ድጋፍ ምሥጋና አቅርበዋል።

ሟቾቹ የራያ ቆቦ ወረዳ አስተዳዳሪና የወረዳው የሰላምና ደህንነት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ግንቦት 23 ቀን 2012 ዓ.ም ከወልዲያ ከተማ ስብሰባ ላይ ቆይተው ሲመለሱ በጥይት ተመተው መገደላቸው ተዘግቦ እንደነበር ይታወሳል።

የአመራሮቹ ግድያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተላልፎ ከሠርግ የሚመለሱ አምስት ሰዎችን ጭኖ ሲጓዝ የነበረ አንድ ባጃጅ ድርጊቱ ለኮሮና ቫይረስ የሚያጋልጥ በመሆኑ ሕግ ለማስከበር እንዲቆም በጠየቁበት ወቅት በተተኮሰ ጥይት የተፈጸመ ነው ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም