በላይ አርማጭሆ ወረዳ ሕገወጥ የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ለቫይረሱ አጋላጭ እንደሆኑ ተጠቆመ - ኢዜአ አማርኛ
በላይ አርማጭሆ ወረዳ ሕገወጥ የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ለቫይረሱ አጋላጭ እንደሆኑ ተጠቆመ
ጎንደር፣ ሰኔ 02/2012 (ኢዜአ ) በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በላይ አርማጭሆ ወረዳ የሞተር ብስክሌትና አነስተኛ የጭነት ተሸከርካሪዎች የሚካሄደው ሕገወጥ የማጓጓዝ እንቅስቃሴ ለኮሮና ቫይረስ አጋላጭ እንደሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ጠቆሙ።
የኮሮ መከላከል ግብረ ኃይል አባል የሆነው የወረዳው ትራፊክ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት በበኩሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ክልከላዎች ጥሰው የተገኙ እስካሁን ከ40 በላይ አሽከርካሪዎች ማስቀጣቱን ገልጿል።
በወረዳው የትክል ድንጋይ ከተማ ነዋሪ አቶ ደሳለው መኳንንት ለኢዜአ እንዳሉት ሮቢትና ጃኒካው ወደ ተባሉት የገጠር ከተሞች ለሰው ጭነት ባልተፈቀዱ ተሸከርካሪዎች በርካታ ሰዎች እየተጓጓዙ ነው።
በአነስተኛ የጭነት ተሸከርካሪዎቹ እስከ 40 ሰው በመጫን ተጓዦችን ለቫይረሱ በሚያጋልጥ ሁኔታ እያጓጓዙ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
መንግሥት አፋጣኝ እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባም አመልክተዋል።
የወረዳው ነዋሪ አቶ መስፍን ሙላት በበኩላቸው በአካባቢያቸው በማጓጓዝ ሕገወጥ ተግባር የተሰማሩ በርካታ ሞተር ብስክሌቶች ለቫይረሱ አጋላጭ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
እያንዳንዱ የሞተር ብስክሌት እስከ አራት ሰዎችን እየጫኑ ስለሚያጓጉዙ ድርጊቱ ተሳፋሪዎችን ለኮሮና በሽታ የሚያጋልጥ በመሆኑ ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል እንዲደረግ ጠይቀዋል።
"ሕገወጥ የጭነት ተሸከርካሪዎቹ እየፈጸሙት የሚገኘው የማጓጓዝ ተግባር በሽታው ከከተማ ወደ ገጠር በፍጥነት እንዲዛመት ሥጋት የሚያሳድር ነው" ያሉት ደግሞ የዚሁ ወረዳ ነዋሪ አቶ ሞላ ክፍሌ ናቸው።
የወረዳው ትራፊክ ፖሊስ የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ማረጋገጫ ክፍል ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር መቅደስ ፈንታሁን በገጠር ከተሞቹ የጭነት ተሽከርካሪዎችና ሞተር ብስክሌቶች ሰዎችን እንደሚያጓጉዙ አረጋግጠዋል።
"ችግሩ የተፈጠረውም መንገዶቹ በመደበኛ የትራንስፖርት ሥምሪት ያልተካተቱና የትራፊክ ፖሊስም ያልተመደበባቸው በመሆኑ የተፈጠረ ነው" ብለዋል።
በዚህም ሕገወጥ አሽከርካሪዎች አጋጣሚውን በመጠቀም ለበሽታው አጋላጭ በሆነ መንገድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ክልከላዎችን በተጻራሪ ሁኔታ እያጓጓዙ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ለመቆጣጠር በተደረገ ጥረትም በድርጊቱ የተሳተፉ ከ40 በላይ አሽከርካሪዎች በቁጥጥር ሥር በማዋል እያንዳንዳቸው እስከ አንድ ሺህ 600 ብር በሚደርስ ገንዘብ እንዲቀጡ ተደርጓል ብለዋል።
ኅብረተሰቡ በሕገወጥ ትራንስፖርት በመጓጓዝ ራሱንና ቤተሰቡን ለኮሮና ቫይረስ ከማጋለጥ እንዲቆጠብ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የመደበኛ ትራንስፖርት ሥምሪት እንዲፈቀድም ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር እየተነጋገሩ መሆናቸውንም አስረድተዋል።