የኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን የውሃ ሚኒስትሮች ዛሬ ማምሻውን የቪዲዮ ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን የውሃ ሚኒስትሮች ዛሬ ማምሻውን የቪዲዮ ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2/2012(ኢዜአ) የኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን የውሃ ሚኒስትሮች በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት ላይ የቪዲዮ ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በባለሙያዎቻቸውና በውሃ ሚኒስትሮቻቸው አማካኝነት ቴክኒካል ጉዳዮች ላይ ውይይት ሲያካሂዱ እንደነበር ይታወሳል።
ይሁንና በተለይ ግብጽ በውይይቱ ጊዜ አቋሟን በመቀያየርና አዳዲስ ሀሳቦችን በማምጣት ውይይቱ እንዲራዘም ከማድረግ ባለፈ ያለውጤት እንዲጠናቀቅና ስታደርግ ቆይታለች።
ግብጽ በግድቡ ውሃ አሞላል ላይ ይዛ በቀረበችው አዲስ ዕቅድ ምክንያት ስምምነት ላይ ባለመደረሱ ሦስቱ አገራት ለአንድ ዓመት ያህል ምንም አይነት ውይይት ሳያደርጉ ቆይተዋል።
በዚህ መሃል በአሜሪካና ዓለም ባንክ ታዛቢነት አገራቱ በግድቡ ውሃ ሙሌት ላይ ውይይታቸውን በድጋሚ በዋሽንግተን መጀመራቸው ይታወሳል።
ይሁንና የአሜሪካ መንግስት ቀደሞ በታዛቢነት አሁን ደግሞ በአደራዳሪነት መግባቱን በመቃወም ኢትዮጵያ በውይይቱ ራሷን አግልላለች።
ምንም እንኳን የሦስቱ አገራት ውይይት መቋጫ ባያገኝም ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ በማፋጠን ከመጪው ሐምሌ ወር ጀምሮ የተወሰነ ውሃ ለመያዝ ዝግጅቷን አጠናቃለች።
የሦስቱ አገራት የውሃ ሚኒስትሮች ዛሬ አመሻሽ ላይ የግድቡ ውሃ ሙሌትን አስመልክተው በቪዲዮ ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ኢዜአ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘው መረጃ ያመለክታል።