የበርበራ ወደብ በኢትዮጵያና ሶማሌላንድ መካከል የንግድ ልውውጡን ያሳልጠዋል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
የበርበራ ወደብ በኢትዮጵያና ሶማሌላንድ መካከል የንግድ ልውውጡን ያሳልጠዋል ተባለ
ሰኔ 2/2012 (ኢዜአ) የበርበራ ወደብ ኮሪደር ግንባታ ኢትዮጵያና ሶማሌላንድን ምጣኔ ሀብታዊ ግንኙነት ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ተገልጿል።
የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሙሳ ቡኪ በዱባዩ ዓለም አቀፍ የወደቦች አስተዳዳር ኩባንያ የሚገነባውን የወደብ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክት መክፈታቸው ታውቋል።
ወደቡ ሶማሌላንድንና የአፍሪካ ቀንድ ሀገራትን ተጠቃሚ ያደርጋልም ተብሏል።
ፕሮጀክቱ 400 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የተያዘለትና የሶማሌላንድ አጎራባችና የኢትዮጵያ የድንበር ከተማ ቶጎጫሌን የሚያስተሳስር መሆኑ ተገልጿል።
በኢትዮጵያና በሶማሌላንድ ወደ 800 ሚሊየን ዶላር ለሚጠጋው የንግድ ልውውጥም ወሳኝነቱ ተነግሮለታል፡፡
የወደብ መሠረተ ልማት ማስፋፊያው አካል የሆኑት የመንገድ ፕሮጀክቶቹ በአቡዳቢ የልማት ፈንድ እየተደገፉ የሚሰሩ እንደሆኑም ተገልጿል፡፡
የሶማሌላንድ የትራንስፖርትና አውራ ጎዳና ልማት ሚኒስትር አቦከር ኦስማን እንዳሉት ይህ አዲሱ መንገድ 11.3 ሜትር ስፋትና ከ40 ቶን በላይ ሊይዝ የሚችል እንዲሁም ዘላቂነት ያለው ነው ብለዋል፡፡
የዱባዩ ዓለም አቀፍ የወደቦች አስተዳዳር የበርበራ ወደብን ለማስተዳደር የ30 ዓመታት ሥምምነት ከሶማሌላንድ መንግሥት ጋር መፈራረሙን የዑጋንዳው ኢስት አፍሪካን ቢዝነስ ዊክ ዘገባ ያመለክታል።
የወደብ ማስፋፊያ ሥራው ሲጠናቀቅ የማስተናገድ አቅሙ በ50 በመቶ ይጨምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ዘገባው ጨምሮ አስታውቋል።