በምስራቅ ሀረርጌ ዞን ሐረማያ ከተማ በደረሰ የትራፊክ አደጋ 2 ሰዎች ሞቱ

ሐረር፣  ሰኔ 02/2012 (ኢዜአ) በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ሐረማያ ከተማ ትናንት ምሽት በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ2 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በሌሎች ሁለት ሰዎች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ ገለፀ።

የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዲቪዥን ተጠባባቂ ሃላፊ  ኢንስፔክተር ቶሎሳ ጎሹ ዛሬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ከዞኑ ግራዋ ወረዳ ጫት ጭኖ ይጓዝ የነበረ ሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3 ኦሮ 26083 አይሱዙ የጭነት መኪና  ከአወዳይ ወደ ሀረማያ ከተማ ይጓዝ በነበረው ኮድ 1 ኦሮ 49050  ባለ ሶስት እግር ባጃጅ ላይ በመውጣቱ  አደጋው ሊደርስ ችሏል። 

ትናንት ከምሽቱ 4 ሰዓት አካባቢ በከተማው ገንደ ቃሹም በተባለው ሰፈር በደረሰው በዚሁ አደጋ የባጃጁ አሽከርካሪና የአንድ ተሳፋሪ ህይወት ወዲያውኑ ሲያልፍ በ2 ሰዎች ላይ ደግሞ  ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።

ከባድ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሁለት ሰዎች ሐረር ከተማ በሚገኘው ህይወት ፋና  ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በህክምና ላይ ሲሆኑ የሟቾቹ አስከሬንም ለቤተሰቦቻቸው ተሰጥቷል።

የአይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪ ሾፌር ለጊዜው በመሰወሩ ፖሊስ ክትትል እያደረገ ሲሆን የአደጋው መንስኤ ከፍጥነት በላይ ማሽከርከር ነው  ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም